ዜና ዜና

ኢትዮጵያ ከውስጥ ጥንካሬዋ አኳያ "በቀጣናው በሚፈጠሩ ሁኔታዎች ስጋት አይገባትም" -ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም

ኢትዮጵያ አሁን ካላት የውስጥ ጥንካሬ አኳያ ሲታይ "በአካባቢያዊ በሚፈጠሩ የጸጥታና የደህንነት ችግሮች ምንም ስጋት አይገባትም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ይህን የገለጹት "ግብፅ በበርበራ ወደብ ወታደራዊ ሰፈር ገንብታላች ይባላል ፣ በኤርትራም ወታደራዊ ሰፈር ለማቋቋም ቦታ አግኝታለች ይባላል።

ይሄ ለኢትዮጵያ ስጋት አይሆንም ወይ?" የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦላቸው ሲመልሱ ነው።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ "በመከባበር ስሜት ብቻ ሳይሆን በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው" በማለት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በፈጠረችው የውስጥ ጥንካሬ በአካባቢያዊ ምንም ዓይነት የጸጥታ ስጋት ቢፈጠርም አንዳች የሚያሰጋ ሁኔታ እንደሌለ ምላሽ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ወቅት "ከግብጽ ጋር መልካም ግንኙነት አለን" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ግብፅ በበርበራ ወታደራዊ ሰፈር መስርታለች የሚለው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን ነው የገለጹት።

ሀሰተኛ ወሬው በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ጥሩ ግንኙነት እንዳይኖር የሚፈልጉ ወገኖች የሚያሰራጩት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያና ግብጽ በመሪዎች ደረጃ ተከታታይ ውይይቶች ሲያካሄዱ መቆየታቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የግብፅ መንግስት በኢትዮጵያ በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሃኖች ላይ "አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ ቃል ገብቶልናል" ብለዋል።

ቀደም ሲል በወሰዱት እርምጃ "የተወሰኑ ሰዎችን ማሰራቸውን ሪፖርት አድርገውልናል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት የሁለቱ አገሮች ግንኙነትን የሚጠናክሩ ስራዎች መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያን የሚጎዳ ማንኛውም እንቅስቃሴ በግብፅ ምድር አይደረግም" በማለት የአገሪቷ መንግስት ቃል ገብቶልናል፤" 'ይሄ እውን ይሆናል' የሚል ተስፋ አለን" ብለዋል።

በውጭ የሚገኙ እና አገር ለማተራመስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመሸጉበት አገሮች በህግ እንዲጠየቁ መንግስት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ጉዳዩ ግን እጅግ የሚያሳስብ ያለመሆኑን ተናግረዋል።

"ሌሎች የአረብ አገሮችም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር የፈለጉት ከጤንነት የተነሳ ነው ወይ?" የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፤ የአረብ አገሮቹ በምስራቅ አፍሪካ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የራሳቸውን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያደርጉት መሆኑን ነው ያብራሩት።

በቀይ ባህርና ባህረ ሰላጤ አካባቢ ሰላማቸውን ለማረጋገጥ፣ በየመን አካባቢ የአልቃይዳ እና በሶማሊያ የአልሸባብ እንቅስቃሴ ከሚፈጥረው ስጋት አኳያ "ሰላማቸውን ለማረጋገጥ የሚያከናውኑት ተግባር እኛን የሚያስፈራ አይሆንም" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም እንዳሉት፤ በርካታ የአረብ አገር መሪዎች ኢትዮጵያን የሚጎበኙት የአገሪቷ ዲፕሎማሲያዊ ተፅእኖ እየጠነከረ በመምጣቱ እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ባለመቻሉ አዲስ ፖሊሲ ተጠንቶ ለሚመለከተው አካል መቅረቡን ገልጸዋል።

ፖሊሲው "እኔ ከሞትኩኝ ሰርዶ አይብቀል" የሚለው የኤርትራ መንግስት አካሄድ እንዳይቀጥልና "በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን የሚያስችል ይሆናልም" ብለዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከጎረቤት አገሮች እና ከአረብ አገሮች ያለውን ግንኙነት እያጠናከረች መሆኑን ገልፀው፤ "ይህን ይበልጥ ለማጠናከር በየጊዜው የፖለቲካ ምክክሩን መቀጠል ያስፈልጋል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከደቡብ ሱዳን በመነሳት በኢትዮጵያ ጥቃት የሚፈጽመው የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ችግርም የሚፈታው የደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ሲሰፍን ነው፣ "ለዚህም አብረን እየሰራን ነው " ብለዋል።

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2009/ኢዜአ/