ዜና ዜና

የከተማዋ የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ ገጽታዋን እየለወጠው ነው-የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች

በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሔደ ያለው የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ የከተማዋን ገጽታ እየለወጠው መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማው የነጭ ሣር ክፍለ ከተማ ውሃ ምንጭ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ሂዲታ ኮይራ እንደተናገሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአረንጓዴ ልማት የተሰጠው ትኩረት የከተማዋን ገጽታ እየቀየረው ነው።

በውበትና ፅዳት ሥራ ለረዥም ጊዜ መስራታቸውን የገለጹት አቶ ሂዲታ ቀደም ሲል ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አሠራሮች ባለመዘርጋታቸው በከተማዋ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ሳይታይ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

"አሁን በባለቤትነት የሚንቀሳቀሱ በርካታ ማህበራት በአረንጓዴ ልማት ተደራጅተው በመስራታቸው እየመጣ ያለው ለውጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት"ብለዋል።

በከተማዋ በመንገድ አካፋዮች የሚደረገው የአረንጓዴ ልማትና የችግኝ ማፍያ ቦታዎች መስፋፋት ጥሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በሸቻ ክፍለ ከተማ የጫሞ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ካሳሁን ካንኮ ናቸዉ ፡፡

"ከደረቅ ቆሻሻ ጋር ተያይዞ በመንደራቸው በየ15 ቀኑ የልማት ዘመቻ መኖሩን ጠቁመው የከተማዋ ነዋሪ ተመሳሳይ ተግባራትን በመፈጸም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል፡፡

በእያንዳንዱ አባወራ ደጃፍ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ዕቃዎች ተዘጋጅተው የመጠቀም ልምዱ እንዲጎለብት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው ለአረንጓዴ ልማት የተሰጠው ትኩረት እንዲጠናከር የሚጠበቅባቸውን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በአረንጓዴ ልማት ተደራጅተው ወደ ሥራ ከገቡ 8 ማህበራት ውስጥ የጭሊሎ አረንጓዴ ልማት ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ይበልጣል ኤሊያስ በበኩሉ እንደገለጸው በዘርፉ መሰማራታቸው የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ከተማዋን አረንጓዴና ውብ ለማድረግ እያስቻላቸው ነው።

በተያዘው ዓመትም 7ሺ 600 ካሬ ሜትር የመንገድ አካፋዮችን ማልማታቸውን ገልጾ ቆሻሻን ወደ ብስባሽ ቀይረዉ ኮምፖስት በማምረት ጥቅም ላይ ለማዋል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም ጠቅሷል።

በአርባምንጭ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅና የአከባቢ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አምሳሉ መውዜሩ በተያዘው በጀት ዓመት በመንገድ አካፋዮች 3 ነጥብ7 ኪሎ ሜትር ሣርና ችግኝ በማህበራት እንዲለማ መደረጉን ገልጸዋል ፡፡

"የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱን ለማዘመን ከከተማው በ7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ ግንባታ እየተጠናቀቀ ነው"ብለዋል።

ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ በመሆኗ ፓርኮችን ፣የትምህርት እና የሃይማኖት ተቋማትን በማልማት የአረንጓዴ ልማቱ ለአከባቢው ህብረተሰብ የሚሰጠውን ጠቀሜታ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

አርባምንጭ ሚያዝያ 12/2009/ኢዜአ/