ዜና ዜና

ክልሉ ሕግ አክብረው ለሚሰሩ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍና ጥበቃ ያደርጋል -የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ

በክልሉ ሕግ አክብረው ለሚንቀሳቀሱ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍና ጥበቃ አንደሚደረግላቸው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አስታወቁ።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ባለሃብቶች ጋር ተወያይቷል።

ባለሃብቶቹ ክልሉ ለኢንቨሰትመንት ከመጋበዝ ባለፈ ቀርቦ በመደገፍና አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ረገድ ክፍቶቶች አሉበት ብለዋል።

በተለይም ኢንቨስትመንቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰፊ የመሠረተ ልማት ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ውሃ፣ መንገድና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን አመልክተዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድም ጉዳዩን በሚያስተባብሩ ከላይ አስከ ታችኛው ደረጃ በሚገኙ ተቋማት ምልልስና እንግልት እንደሚገጥማቸው አስረድተዋል።

ባለሃብቶቹ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ የተሰጠው ትኩረት እንዳለ ሆኖ አሁንም ከክልሉ የቆዳ ስፋት ጋር ተመጣጣኝ ስራ ሊፈጠር ይገባል ነው ያሉት።

የክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲያድግ ከተፈለገ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በዘላቂነት ሊፈቱ ይገባልም ብለዋል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በቅርቡ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተናግረዋል።

የመሠረተ ልማት አቅርቦትን በተመለከተ ክልሉ አቅሙ የሚችለውን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ለመፍታት ባለሃብቶቹም ከመንግስት ጋር መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ በክልሉ ከ10 ሺህ በላይ ባለሃብቶች የሚገኙ ቢሆንም ወደ ስራ የገቡት 46 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።

አብዛኞቹ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ስም የወሰዱትን መሬት ከ10 ዓመት በላይ አጥረው በማስቀመጥና ለሌሎች አገልግሎቶች እያዋሉት መሆኑን ጠቁመዋል።

ክልሉ ለባለሃብቶቹ መሬት ሲሰጥ ዋጋ ከፍሎ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ የወሰዱትን መሬት በአግባቡ የማይጠቀሙ ባለሃብቶች ላይ "እርምጃ ይወሰዳል" ነው ያሉት።

ሕጉን አክብረው የአካባቢውን ማህረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ለሚንቀሳቀሱ ባለሃብቶች የሚደረገው ማበረታቻና ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማና ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብይ አህመድ በበኩላቸው በባለሃብቶቹ የተነሱት ችግሮች እየተፈቱ የሚሄዱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የክልሉ መንግስት እስካሁን ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያደረጋቸውን ጥረቶች መመልከት ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ፍጹም አረጋም መንግስት የአገር ውስጥ ባለሃብቱን እያበረታታ በርካታ ውጤቶችንም እያስመዘገበ መምጣቱን አስረድተዋል።

በተለይ ልማታዊ ባለሃብቶች ተለይተው አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አክለዋል።

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2009/ኢዜአ/