ዜና ዜና

የክልሎቹን አለመግባባት ለመፍታት በአጎራባች አካባቢዎች የልማት ሥራዎች ይሰራሉ

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ከወሰን ማካለል ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን አለመግባባት በመፍታት አጎራባች አካባቢዎችን ለማልማት እንደሚሰሩ የክልሎቹ ርዕሰ መስተዳድሮች ተናገሩ።

በሁለቱ ክልሎች መካከል ከወሰን ማካለል ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት የሚያስችል አስተዳደራዊ የወሰን ማካለል ሥምምነት ትናንት ተደርሷል።

በሥምምነቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድን ጨምሮ የክልሎቹ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ሥምምነቱ ቀደም ሲል በወሰን ማካለል ጋር በተያያዘ የተጠናቀቁ ሥራዎች ላይ ተጨማሪ ተግባራትን ለማከናወንና አለመግባባቶችን በዘላቂነት ማስቀረትን ዓላማ ያደረገ ነው።

በሁለቱ ክልሎች መንግሥታት የፌዴራል አካላትና በሕዝቡ የጋራ ጥረት ሥምምነት ላይ ደርሰው ወደ ተግባር የገቡትን አካባቢዎች የወሰን ማካለል ሥራም ይጨምራል።

ስምምነቱ በሰባት ዞኖች 33 ወረዳዎች ሥር በሚገኙ 147 ቀበሌዎችና መንደሮች መካከል አስተዳደራዊ ወሰን ማካለልንም ያጠቃልላል።

ይህን ሥምምነት ተከትሎ ርዕሰ መስተዳድሮቹ ግጭት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ዘላቂ ልማት በማረጋገጥ አለመግባባቶችን ከመሰረታቸው ለመፍታት እንደሚሰሩ ነው ያረጋገጡት።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድ እንደተናገሩት ሁለቱ ክልሎች በሃይማኖት፣ በቋንቋና ባህል የተጣመሩ በመሆናቸው የሚያጋጭ ምክንያት የላቸውም።

የሁለቱ ክልሎች ግጭት በዋነኝነት በተፈጥሮ ጫና የተነሳ በአካባቢው ልማት ባለመኖሩና ከድህነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው አቶ አብዲ የተናገሩት።

ለዚህም ደግሞ በአካባቢው በተለይም የውሃና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት የአካባቢውን የልማት ጥያቄ በዘላቂነት በመፍታት ግጭቶችን ለማስቀረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ይህም ለአካባቢዎቹ ብቻ ከሁለቱ የክልል መንግሥታት በጀት በመፍቀድ እንደሚከናወን አቶ አብዲ አረጋግጠዋል።

የተደረሰው ሥምምነት ለሕዝቡ ችግር ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥና በተለይም ለአመራሩ ትልቅ ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው በክልሎቹ መካከል ያለው የመሬት ችግር አይደለም፣ ሁለቱም ክልሎች ከበቂ በላይ የመሬት አቅርቦት አላቸው ይላሉ።

ይሁንና ሁለቱ ክልሎች የሚጋሯቸውን አካባቢዎች በማልማትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን እንደሚንቀሳቀሱና አለመግባባቶችን ለመፍታት በጋራ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

አካባቢው ለዘመናት ልማት ተነፍጎ ቆይቷል፤ ይህንን ለመቀልበስ የልማት ሥራዎችን በሥፋት በመሥራት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ኑሮ መቀየር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ያደረጉ ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ እንደሚሰራ የፌዴራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።
አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2009