ዜና ዜና

ቻይና ለኢትዮጵያ መሰረተ ልማት የምታፈሰው መዋእለንዋይ እየጨመረ ነው

ቻይና ለኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያዎች የምታፈሰው መዋእለንዋይ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መሆኑን ቦርገን መጋዚን ድረገፅ አስነበበ።

ከአውሮፓውያኑ ሚሊኒየም መባቻ በኋላ ቻይና ለአፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በታች ላሉ ሃገራት በሰጠችው ልዩ ትኩረት በርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን ለመሰረተልማት ማስፋፊያ ግንባታዎች በመመደብ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡

በኢትዮጵያም እ.ኤ.አ ከ2009-2012 ባሉት አመታት በድምሩ 4.7 ቢሊየን ዶላር ፈሰስ መደረጉን የብሩኪንግስ ተቋም ሪፓርትን ዋቢ አድርጎ ድረገጹ ዘግቧል።

በህዝብ ብዛቷ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን የምትይዘው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2003-2015 በአማካይ 10.8 በመቶ እድገት ማርጋገጥ መቻሏን ያነሳው ድረገጹ በቀን ከ1.90 ዶላር በታች በማግኘት በፍፁም ድህነት ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ቁጥር በ2000 ከነበረበት 55.3 በመቶ በ2011 ወደ 33.5 በመቶ መቀነሱን ዘግቧል ።

መሰረተ ልማት ባልተዳረሰባቸው ታዳጊ ሃገራት የህዝቦች እና የሸቀጦች እንቅስቃሴ የተፋጠነ እንዲሆን የመንገድና የባቡር መስመሮች መስፋፋት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ያወሳው ዘገባው ባለፈው ጥር ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን የኢትዮጰያና የጅቡቲ የምድር ባቡር መስመር ለአብነት አንስቷል።

እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ የቻይና አፍሪካ ምርምር ተቋም ግምት ቻይና 752 ኪሎሜትር ለሚረዝመው ለኢትዮጵያና ጅቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ 2.49 ቢሊየን ዶላር ብድር ማቅረቧን ገልጿል፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጭም 4 ቢሊየን ዶላር መሆኑን ያነሳው ዘገባው የባቡር ፕሮጀክቱ ወጭና ገቢ ንግዷን በጅቡቱ ወደቦች ላይ ላደረገችው ኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም እንዳለው አስፍሯል ።

ቻይና የምታፈሰው መዋእለንዋይ በባቡር ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ የተወሰነ አለመሆኑ እና በኢትዮጵያ ከሚገነቡ መንገዶች ውስጥ አብዛኛዎቹ በቻይና ታላላቅ ኩባንያዎች ከመያዛቸውም በላይ ቻይናውያኑ ኢትዮጵያ በሁለተኛው የእድገትና ሽግግር እቅድ ለምታልመው የኢንዱስትሪ መር ምጣኔ ሃብት ግንባታ የሚሆኑ ግዙፍ የማምረቻ ማእከላት ማስፋፋት ላይም እየሰሩ መሆኑንም ዘገባው አስታወሷል።

ሚያዝያ 12/2009 / ኢዜአ/