ዜና ዜና

የጎንደር ከተማ የመንግስት ሰራተኞች ለ7ኛው የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም መሳካት እንደሚሰሩ ገለጹ

በጎንደር ከተማ በሚካሔደው 7ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን በመቀበል ለፎረሙ መሳካት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ በከተማዋ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ዛሬ ለመንግስት ሰራተኞች ባዘጋጀው መድረክ ላይ የፎረሙን ዋና አላማ፤እየተደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅትና የአፈጻጸም ደረጃ አስመልክቶ ገለጻ አድርጓል።

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ብስራት ጋሻው ፎረሙ ተቀዛቅዞ የቆየውን የከተማውን የንግድ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዘርፍ በማነቃቃት በኩል ታላቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

"ለፎረሙ ዝግጅት ተብለው የተጀመሩ የመንገድ፤ የጽዳትና ውበት፤ የመዝናኛ ስፍራዎች ግንባታ፤ የኮብል ስቶን የድንጋይ ንጣፍ የልማት ስራዎች የከተማውን መልካም የልማት ገጽታ የሚያጎሉ በመሆናቸው ዘላቂና ቀጣይነት ባለው መንገድ ሊገነቡ ይገባል" ብለዋል፡፡

አቶ አደራጀው አዳነ የተባሉ የመንግስት ሰራተኛ በበኩላቸው "ከተማዋ የምትታወቅባቸውን የቱሪዝም ሀብቶች በማስተዋወቅ የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር አጋጣሚውን መጠቀም ተገቢ ነው" ብለዋል፡፡

የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ጽዳት በመጠበቅና ጎብኚዎችን በተገቢው መንገድ ማስተናገድ እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም የሚሳተፉበት ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል።

"ፎረሙ የከተማዋን መልካም ገጽታ ለመገንባት ትልቅ ድርሻ አለው" ያሉት ደግሞ ሌላው የመንግስት ሰራተኛ አቶ መርከብ እሸቴ ናቸው፡፡

ፎረሙን ምክንያት በማድረግ በከተማው እየተሰሩ ያሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የነዋሪውን የረጅም አመታት የልማት ጥያቄ ምላሽ በመስጠት በኩል የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የመሰረተ ልማት ስራዎቹ ከፎረሙ ማብቂያ በኋላም ቀጣይነት ሊኖራቸው እንደሚገባና ዘላቂ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ ጥራታቸው ተጠብቆ ሊካሄዱ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ለፎረሙ ስኬታማነትም ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶችን ከመቀበል ጀምሮ ፎረሙ ያለ አንዳች ስጋት በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑም አቶ መርከብ ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል ፎረሙን በማሳካት በኩል የከተማ አስተዳደሩ አደረጃጀቶችን ፈጥሮ ወደ ተግባር በመግባት የተጀመሩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በአብዛኛው በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የልማት ስራዎቹ ምንም እንኳን ፎረሙን ምክንያት በማድረግ የተጀመሩ ቢሆንም በበጀት አመቱ በከተማው ሊሰሩ የታቀዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለፎረሙ መሳካትም የመንግስት ሰራተኛው ከመላው የከተማው ህዝብና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን እንዲረባረብም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አየልኝ ሙሉአለም በበኩላቸው የከተማውና የዞኑ አስተዳደር 7ኛውን የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም በስኬት ለማጠናቀቅ የጋራ ሃላፊነትና ተልዕኮ ወስደው በርካታ ተግባራትን በቅንጅት እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ፎረሙ ከተማዋና ዞኑ ለተሳታፊው የሚተዋወቁበት ፣እንግዶችም ከፎረሙ መልስ የጎንደር አምባሳደር በመሆን መልካም ገጽታዋን ለሌሎች የሚያካፍሉበት ምቹ አጋጣሚ በመሆኑ የመንግስት ሰራተኛው ለስኬታማነቱ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ፎረሙን አስመልክቶ ለግማሽ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ በከተማው ከሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

"የከተሞች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር ለህዳሴአችን" በሚል መሪ ቃል በሚካሔደው የከተሞች ፎረም ላይ ከ200 በላይ የሀገር ውስጥና 40 ያህል የውጪ ሀገር እህት ከተሞች፤የንግድ ኩባንያዎች፤ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከ15ሺ በላይ እንግዶችም እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

ጎንደር ሚያዚያ 11/2009/ኢዜአ/