ዜና ዜና

ለመኸር እርሻ አገልግሎት የሚውል የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት እየቀረበ ነው

ለዘንድሮው የመኸር እርሻ አገልግሎት የሚውል የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት እየቀረበ መሆኑን የእርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ለ2009/2010 የመኸር እርሻ አገልግሎት የሚውል ከ15 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት ለማቅረብ እቅድ መያዙንም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

በሚኒስቴሩ በብዜት የሚቀርቡ ግብዓቶች ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ እንዳለ ጉደታ እንደገለጹት ሀገራዊ የእርሻ ሥራ ዕድገትን ግብ ለማሳካት በዘንድሮው የምርት ዘመን ለእርሻ ሥራ በግብዓትነት የሚቀርቡ የምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ዋነኛው ተግባር ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡

ለአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ከ9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዟል፡፡

በዚህም የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ከተያዘው ከ13 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ እቅድ ውስጥ ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚሆነው ተገዝቶ ወደብ ላይ ደርሷል፡፡ እስካሁንም 4 ሚሊዮን 492 ሽህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሃገር ውስጥ ተጓጉዞ ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በብርዕ፣ አገዳ ፣ጥራጥሬ ፣ቅባትና ሌሎች ሰብሎች በተመሰከረለት የምርጥ ዘር አቅርቦት በኩልም የክልሎችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በእቅድ ከተያዘው ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ውስጥ እስካሁን በክልልና በፌደራል ዘር አባዥዎች ከ1 ሚሊዮን 225ሺ ኩንታል በላይ መቅረቡን አቶ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

እቅዱን ለማሳካትም በዘርፉ የተሰማሩ የፌደራልና የክልል ዘር አባዥ ድርጅቶች እና የግብርና ምርምር ተቋማት መጠናከር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የዘር ሽያጭን በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ አርሶ አደሩ በወቅቱ ገዝቶ መጠቀም እንዲችል የዘር ቀጥታ ሽያጭ አሠራር ሥርዓት ተዘርግቶ በመለመድ ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ13 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በማረስ ከ345 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እቅድ ተይዟል፡፡

ሚያዝያ 12/2009/ኢዜአ/