ዜና ዜና

ኢትዮጵያና ግብፅ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመስራት ተስማሙ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ወደ ግብፅ በማቅናት ከአገሪቱ ኘሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ እና ከግብፁ አቻቸው ጋር በሁለትዮሽ ትብብር ዙሪያ መክረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በኢቢሲ ስቱዲዮ በመገኘት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ቃል አቀባዩ እንዴገለፁት በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገው ውይይት ገንቢና በመግባባት መንፈስ የተደረገ ነበር፡፡

አገራቱ ያላቸውን ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ ግንኙነት ወደተሻለ ምእራፍ ለማሻገር በየ2 ወሩ በሚንስትሮች ደረጃ ተገናኝተው ለመምከር እንዲሁም በሁሉም ደረጃ የምክክርና የውይይት መድረኮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በሁለቱ አገራት ህዝቦች ከጥርጣሬ የፀዳ መካልም ግንኙነት እንዲኖራቸው ለማድረግ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

የግብፅና ኢትዮጵያ እድገት አንዱ በሌላው ላይ የተመረኮዘ በመሆኑም ለጋራ ልማት በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ጉብኝቱን ያደረጉት ከግብፁ አቻቸው ሳሚሹክሪ በተደረገላቸው ግብዣ እንደሆነ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የሚመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በግብፅ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ካይሮ ማቅናቱ ይታወሳል።

ሚያዝያ 12፣ 2009/ኢቢሲ/