ዜና ዜና

የኮሚሽኑ የምርመራ ውጤት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን መሰረት ያደረገ ነው

በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ስለነበረው ሁከት ያቀረበው የምርመራ ውጤት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን መሰረት የያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ።   

 ኮሚሽኑ በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ ስለነበረው ሁከትና ግርግር ባቀረበው ሪፖርት ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። 

 ኮሚሽነሩ ዶክተር አዲሱ ገብረ እግዚአብሄር እንደተናገሩት ኮሚሽኑ በህገ መንግስቱ መሰረት የሠብዓዊ መብት ጥሰቶችን ገለልተኛ ሆኖ የማጣራት ኃላፊነት ተጥሎበታል። 

 በዚሁ መሰረት በሦስቱ ክልሎች በተከሰተው ግጭት ዙሪያ ህጉንና ሚዛናዊነቱን ጠብቆ ምርመራ አካሂዷል።     

 የምርመራ ውጤቱን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ የምርመራ ሂደቱ በዓለም አቀፍ ህግጋት የተቃኘ እንዲሆን መደረጉንም ተናግረዋል።   

 የምርመራ ሪፖርቱን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ከሆስፒታሎች፣ ከፖሊስና ከፍትህ አካላት፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከመንግስት አካላት መረጃዎችና ማስረጃዎች የማሰባሰብ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።       

 ለምርመራ የሚሰማሩ ባለሙያዎች ተገቢውን ግንዛቤ እንዲጨብጡ ከማድረግ ባለፈ ስነ ምግባሩንና ምስጢራዊነቱን ጠብቀው እንዲሰሩ መደረጉንም ገልጸዋል።   

 የኮሚሽኑ ሪፖርት ምን ያህል ገለልተኛ ነው? ተብለው የተጠየቁት ዶክተር አዲሱ "ኮሚሽኑ የሠብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን የሚያረጋግጠው እንደ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች አየር በአየር ሳይሆን መሬት ላይ ከህዝብ ጋር አብሮ በመስራት ነው" ብለዋል።  

 ገለልተኝነት የሚለካው በተግባር መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ባለፈው ዓመት የቀረቡለትን የግለሰብና የቡድን መብት ጥያቄዎች መርምሮ ምላሽ እንዲሰጥበት በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።  

 ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አኳያም ኮሚሽኑ በጥንቃቄ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለደረሰው የቃጠሎ አደጋ ተጠያቂ አካላትን ለይቶ ውሳኔ እንዲሰጥ ማድረጉን አንስተዋል።  

 ኮሚሽኑ በቀጣይ በክልሎቹ እንዲስተካከሉ ያቀረባቸውን ምክረ ሀሳቦች ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ የክትትል ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።   

 ምክትል ኮሚሽነር እሸት ገብሬ በበኩላቸው ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በየአካባቢው አሰራሮች ተዘርግተው እንቅስቃሴ መደረጉን ተናግረዋል።

  በአገሪቷ  በሦስቱ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ግርግር የ669 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና 20 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችም ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አመልክቷል።

 ኮሚሽኑ በ2008 ዓ.ም በኦሮሚያና በቅማንት ጉዳይ ተመሳሳይ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡም ይታወቃል።

ኢዜአ  ሚያዚያ 11/2009