ዜና ዜና

በኢሉአባቦር ዞን የቅመማ ቅመም ልማት እየተስፋፋ ነው

 በኢሉአባቦር ዞን የቅመማ ቅመም ሰብል ልማት ለማስፋፋት እየተደረገ ያለው ጥረት የዞኑ ዓመታዊ ምርት እንዳሳደገው የዞኑ ቡና ሻይና ቅመማቅመም ልማት ባለስልጣን ገለጸ፡፡

ለቅመማ ቅመም ሰብል ልማት ትኩረት በመስጠት ገቢያቸውን ለማሳደግ  በመስራት ላይ መሆናቸውን በዞኑ  የበቾና መቱ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

በባለስልጣኑ የቅመማ ቅመም ልማት ባለሙያ አቶ ቡላ ገብሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ 13 ወረዳዎች የሚገኙ ከ25 ሺህ በላይ አርሶአደሮች   ኮረሪማ፣ ዝንጅብል፣እርድ ፣በርበሬና ለሌሎችም  የቅመማ ቅመም ሰብሎችን በማልማት ላይ ተሰማርቷል፡፡

አርሶ አደሮቹ ባለፈው መኸር ወቅት ከ5 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በቅመማ ቅመም ሰብሎች በመሸፈን  ከ25 ሺህ 100 ኩንታል በላይ ምርት ሰብሰበዋል፡፡

በወቅቱ የሰበሰቡት ምርት መጠን ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ13 ሺህ ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው ነው።

የምርት መጠኑን  ሊጨምር የቻለው አርሶአደሮች የሚደረግላቸውን ድጋፍና እገዛ በመጠቀም ከደንና ከቡና ልማት ጋር አቀናጅተው ቅመማቅመም የማምረት ስራቸውን በማስፋፋታቸው መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል።

አርሶአደሮች ገበያ ተኮር የቅመማቅመም ሰብሎች በስፋት በማልማት ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ የግብርና ባለሙያዎች በቅርበት የሙያ ድጋፍና እገዛ እያደረጉላቸው መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ፡

"ምርቱን ይበልጥ ለማስፋፋት ሁለት የችግኝ ጣቢያዎች ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ ከ70 ሺህ በላይ ችግኞች አርሶ አደሮቹ እየተባዙ ናቸው " ብለዋል፡፡

አዳዲሶቹ የቅመማቅመም ዝሪያዎች በሔክታር  ይገኝ የነበረው የእርድ ምርት ከ70 ኩንታል ወደ 125 ኩንታል ፣ የኮረሪማ ምርት ደግሞ ከ6 ኩንታል ወደ 8 ኩንታል ከፍ የማድረግ አቅም እንዳላቸውም ተመልክቷል፡፡

አርሶ አደር ጌታሁን ገብረሚካኤል በበቾ ወረዳ ወልጋይ የቁብሳ ቀበሌ ነዋሪ  ሲሆኑ  ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ ከቡና ጋር በጥምር  ኮረሪማ በማልማት ላይ መሆናቸውን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

" ዘንድሮ ከልማቱ 18 ኩንታል እርጥብ ኮረሪማ ሰብስቤያለሁ" ያሉት  አርሶ አደሩ በደንብ ሲደርቅ ከስድስት ኩንታል በላይ እንደሚሆንና  በዚህም  ከ40ሺህ ብር በላይ ገቢ አገኝብታለሁ ብለው እንደሚጠብቁም ጠቁመዋል፡፡

በመቱ ወረዳ የሳርዶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር  ምትኩ ሞርካ በበኩላቸው ከሌሎች ውጤታማ አርሶአደሮች ባገኙት ልምድ በመነሳት በመጪው ክረምት ሩብ ሄክታር የሚሆን መሬት በእርድ ለመሸፈን ዝግጅት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

በመጪው ክረምት የተሳታፊ አርሶአደሮችን ቁጥር ወደ 35 ሺህ በማሳደግ 6ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት በቅመማቅመም ለማልማት መታቀዱን የዞኑ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ባለስልጣን አመልክቷል።

ኢዜአ 08/ 8/2009