ዜና ዜና

የግድቡ ስድስተኛ ዓመት በተለያዩ አገራት ተከበረ

በአፍሪካና በእስያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች አከበሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በዓሉ በኬኒያ፣ ሱዳን፣ ግብጽና ደቡብ ኮሪያ ተከብሯል።

በኬኒያ ናይሮቢ የኢትዮጵያ ባለ-ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳሉት ግድቡ በኢትዮጵያ ህዝብ አቅም እየተገነባ ያለና ሁሉም ዜጋ ታሪካዊ አሻራውን የሚያሳርፍበት ነው።
ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ባሻገር ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር የሚኖራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋል ብለዋል።

ዕለቱን አስመልክቶ በናይሮቢም በተካሄደ የቦንድ ሽያጭ 5 ሺህ 400 የአሜሪካን ዶላር ለግድቡ ግንባታ መገኘቱን መግለጫው አመልክቷል።
በተመሳሳይም በሱዳን ካርቱም ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በዓሉ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ተከብሯል።

የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ ባጸደቁት ሕገ-መንግሥት የተደነገገውን የኢኮኖሚ መርሆዎችን እውን የሚያደርግ፣ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑ በበዓሉ ላይ መገለጹን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በተጨማሪም የግድቡ ግንባታ ከፍተኛ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ አንድምታ ያለው ልማታዊ ክንውን እንደሆነም በመጥቀስ፤ ከስጦታ፣ ከቦንድ ሽያጭና ከሎቶሪ 12 ሺህ 100 የአሜሪካ ዶላር በበዓሉ ስነ-ስርዓት ላይ መሰብሰቡን ጠቁሟል።

በዓሉ በግብፅ ካይሮ በተለያዩ ዝግጆች ሲከበርም ባለ-ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ እንደተናገሩት ግድቡ በአገሪቱ እየተገነቡ ላሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የኃይል ፍላጎት የሚያሟላ፣ የገጠር የኤሌክትሪክ ሽፋንም የሚያሳድግ ነው።

''የቀጣናውን አገራት ትስስር ለማጠናከር ታልሞ እየተገነባ ያለ ግድብ ነው'' ሲሉም ገልጸዋል።
በዓሉ በኮሪያ ሪፐብሊክ ቹንቾን፣ ዴጆን፣ ዴጉ፣ ቡሳንና ሴዑል ከተሞችም በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩን የሚኒስቴሩ መግለጫ አመልክቷል።

አዲስ አበባ ሚያዝያ 4/2009(ኢዜአ)