ዜና ዜና

በገጠር መሬት ኢንቨስትመንት የሚፈጸሙ ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ ይገባል..... የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

 በገጠር መሬት ኢንቨስትመንት የሚፈጸሙ ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግሩን ማፋጠን እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ።

በገጠር ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚመክሩበት መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በክልሉ ሰሜንና ምዕራብ ወረዳዎች ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሰፋፊ መሬቶች መኖራቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የመሬት ሃብትን በተገቢው መንገድ በማልማት ለአገራዊ እድገቱ ማዋል እንደሚገባ አመልክተዋል።

የክልሉን ምርታማነት ለማሳደግ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች በዓለም ላይ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን፣ እውቀትንና ዘመናዊ የግብርና አሰራሮችን በማምጣት የራሳቸውንም ሆነ የአርሶአደሩን የአመራረት ዘይቤ መለወጥ እንዳለባቸው እስገንዝበዋል።

አቶ ገዱ እንዳሉት መንግስትና ሕዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ለሚገኙ ውሱን ባለሃብቶች የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል።

በሌላ በኩል የገቡትን ውል የማያከብሩ፣ ማህበራዊ ኃላፊነትን የማይወጡና በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር የተዘፈቁ ባለሃብቶችን በመለየት የማስተካከያ ርምጃ እንደሚወሰድ አመልክተዋል።

በተለይ በኢንቨስትመንት ስም የሚፈጸሙ ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግሩን ማፋጠን አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

የምክክር መድረኩ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችና የችግሮችን ምንጭ ከመለየት ባለፈ ለመፍትሄው በላድርሻ አካላት የጋራ መግባባት የሚፈጥሩበት እንደሆነም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጸጋ አራጌ በበኩላቸው በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ከአንድ ሺህ 900 በላይ ባለሃብቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ባለሀብቶቹ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ለሚደርሱ ሥራ አጥ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ነው ያስረዱት።

አቶ ጸጋ እንዳሉት፣ ባለሃብቶቹ ምርታማነትን በማሳደግ የክልሉ ልማት እንዲፋጠን፣ ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና ልምድና ተሞክሮን በማምጣት ባለፉት ዓመታት የድርሻቸውን ተወጥተዋል።

በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደስራ ከገቡት ውስጥ ከ 97 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሰብል ማምረት ሥራ መሰማራተቸውን ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ የገለጹት ደግሞ በቢሮው የገጠር ኢንቨስትመንት የሥራ ሂደት መሪ አቶ ኡመር ጣሂር ናቸው።

ባለፈው ዓመት ከአበባ ልማት ብቻ 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ጠቅሰው፣ ከሰብል ልማት ውጭ ያሉ ዘርፎች ውጤታማ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

በዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በሚያስገኙና ሰፊ የሥራ ዕድል በሚፈጥሩ የአበባ፣ የደን፣ የምርጥ ዘር ብዜት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የአግሮ ኢንዱስትሪ ልማት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥራቸው ዝቅተኛ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተጨማሪም "በውል የወሰዱትን መሬት አለማልማት፣ ለሌላ ማከራየት፣ ከአርሶ አደሩ የተለየ አመራረት ዘይቤን አለመከተል የተስተዋሉ ችግሮች ናቸው" ሲሉ በጥናቱ አቅርበዋል።

አቶ ኡመር እንዳሉት፣ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት መሰረት በግብርና ኢንቨስትመንት ከሚጠበቀው 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ባለይ ምርት በአሁኑ ወቅት የተመረተው 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነው።

በጎንደር ከተማ ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው ኮንፈረንስ  ባለሃብቶች፣ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ኢ.ዜ.አ ባህር ዳር መጋቢት 9/2009