ዜና ዜና

ድርጅቱ ለአምስት ዓመታት ያከናወነው የመድሃኒት ተደራሽነትና አገልግሎት ጥራት የማሻሻል ስራ ውጤታማ መሆኑን ገለጸ

የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤይድ) በኢትዮጵያ ለአምስት ዓመታት ያከናወነው የመድሃኒት ተደራሽነትና አገልግሎት ጥራት የማሻሻል ስራ ውጤታማ እንደሆነ ገለጸ።

በአጠቃላይ ሥራውን ለማከናወን 17 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉም ገልጿል።

ድርጅቱ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለአምስት ዓመታት ያከናወነው መርሃግብር መጠናቀቁን አስመልክቶ ትናንት ውይይት ተካሂዷል።

'ለተሻለ የመድሃኒት ተደራሽነትና አገልግሎት ሥርዓት' ወይም 'ሳያፕስ' በሚል በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት  በድርጅቱ አማካኝነት ተግባራዊ ተደርጓል።

የ'ሳይፕስ' ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ታደገ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ከመድሃኒት አስተዳደር ጋር ተያይዞ የአቅም ውስንነትና የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት አለ።

ከዚህ በተጨማሪ መድሃኒት ቤቶች የመረጃ አያያዝ ክፍተት፣ በህክምና ባለሙያ ያልታዘዘ መድሃኒት መጠቀም እንዲሁም ከታማሚው ይልቅ በመድሃኒት ላይ ማተኮር የመሳሰሉ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተመልክቷል።

'ሳይፕስ' የመድሃኒት አስተዳደር አቅምን ማሳደግ፣ የአገልግሎት ጥራት መጨመርና የመረጃ ልውውጡን ማጎልበት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን ነው የገለጹት።

ከተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትም የድህረ ምረቃ ትምህርት እንዲሰጥ ጥረት መጀመሩንም ገልጸዋል።

በዚህም በዘርፉ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮችን በማቃለል ረገድ "የተሻሉ ለውጦች ማምጣት ችለዋል" ብለዋል ዳይሬክተሩ።

ከነዚህ መካከል በመድሃኒት ተደራሽነት ዙሪያ በተወሰነ መልኩ በአገሪቷ ግልጽነትና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማምጣት መሞከሩን ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ ቁሳቁስ የማሟላት፣ መድሃኒቶች ደረጃ እንዲወጣላቸው የመስራት፣ ደንቦችና አሰራሮች እንዲዘጋጁና መድሃኒቶች ኦዲት የማድረግ ተግባራት እንዲከናወኑ መደረጋቸውን አስረድተዋል።

በጥቅሉ ስራው የመድሃኒት ብክነትና ሙስና መቀነስ ያስቻለ፣ ስምንት መቶ ሙያተኞችን ማሰልጠን የተቻለበትና የተለያዩ ዘመናዊ የመድሃኒት ማስቀመጫ ቁሳቁሶች የተገኙበት መሆኑንም አመልክተዋል።

ኢ.ዜ.አ አዲስ አበባ መጋቢት 9/2009