ኢኮኖሚ ኢኮኖሚ

ኢኮኖሚ

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዋነኛነት በግብርና ዘርፍ የተያዘ ነው ከዚህም ከሀገሪቱ ጠቅላላ የውስጥ ምርት 45 ከመቶውን ይሸፍናል፣ 10 ከመቶ የሚሆነው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ሲሆን፣ 13.3 ከመቶው ደግሞ የማምረቻው ዘርፍ ይይዛል፡፡ የወጪ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ የሚከናወን ሲሆን ከዚህም ውስጥ እስከ 60 ከመቶ የሚደርሰው የቡና መላክ ወጪ ንግድ ነው፡፡

ግብርና

እርሻ የአገሪቱ የጀርባ አጥንት ሲሆን አገሪቱ ከዚሁ የኢኮኖሚ ዘርፍ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ስኳር እና የከብት መኖ ወደ ውጭ ትልካለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣ የከብት ሀብት ልማት በመኖሩ ከዚህ ዘርፍ የቁም ከብት፣ ቆዳና ሌጦ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ታገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ ካሏት አጠቃላይ ዘርፎች ውስጥ የግብርና ዘርፍ ቀዳሚውን ሲይዝ በ2006/07 ዓ.ም በተገኘ አመታዊ ስሌት መሰረት ግብርና 45.9 ከመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱ የምርት ውጤት ይሸፍናል፡፡ ወደ 45 ከመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ መሬት ለግብርና ስራ ምቹ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ወደ 10‚556 ሄክታር መሬት ብቻ ለእርሻ አገልግሎት የዋለ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግብርና በመሪነት የሚገኝ ዘርፍ ሲሆን ፤ ለሀገሪቱ የሚሆነውን የምግብ ፍጆታ ከማቅረቡም በላይ የተለያዩ ጥሬ እቃ አቅርቦቶችን ለኢነዱስትሪው ዘርፍ በማቅረብ እንዲሁም ወደ ውጭ በመላክ ለሀገሪቱ እስከ 86 ከመቶ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት የሀገሪቱ ብሄራዊ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ግብርና ላይ የቆመ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዘርፉ 85 ከመቶ የሚሁነውን የሀገሪቱ የሰራተኛ ሀይል ይይዛል እንዲሁም 70 ከመቶ የሚሆነውን የሀገር ውስጥ ኢንዱሰትሪዎች የጥሬ እቃ ፍላጎት ይሸፍናል፡፡

ይህንን ሁኔታ በመመልከት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ከተ.መ. የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር የግብርና ምርቶችን ገበያ ለማፈላለግ እና ለማሳለጥ እንዲረዳ የኢትዮጵያ የምርት ገበያን አቋቁሟል፡፡ በዚህም አሰራር የግሉ ልማት ዘርፍና ትናንሽ ገበሬዎች እንደሚሳተፉና ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡

የአምራች ዘርፍ

በ2006/07 ዓ.ም 13.3 ከመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ጠቅላላ ምርት ያስመዘገበው ይህ ዘርፍ ነው፡፡ ከዚህም ዘርፍ የምግብ፣ የለስላሳ መጠጦች፣ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳና ሌጦ ውጤቶች ይገኙበታል፡፡ ከቅርብ አመታት ወዲህ የፈነዳውን ከፍተኛ የግንባታ ስራዎች እንቅስቃሴ ለማገዝ እንዲሁም በዚሁ ምክንያት የተከሰተውን የሲሚንቶ አቅርቦትን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ በሆነ የኢንቨስትመንት ፍሰት የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ዘርፉ በዋነኛነት ከግብርና የሚገኙ ምርቶችን ለማቀነባበር እና ለማምረት ይንቀሳቀሳል፡፡ በዚህም ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚውሉ የሸማቾች እቃዎችን ያቀርባል፡፡ ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶችም ጨርቃ ጨርቅ፣ የታሸገና የቀዘቀዘ ስጋ፣ በከፊል የተጨረሱ ቆዳና ሌጦ፣ ስኳርና ሞላሰስ፣ የእግር አልባሳት፣ ትንባሆ፣ ለስላሳ መጠጦች፣ ዘይት፣ ሰም ፣ ሌዘርና የሌዘር ውጤቶችን ያቀርባል፡፡

አገልግሎት ሰጪ ዘርፍ

የአገልግሎት ሰጪ ዘርፍ 40.5 ከመቶ የሚሆነውን የሀገር ውስጥ ምርት ይሸፍናል፡፡ ይህ ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ቀስ በቀስ በማደግ ላይ የሚገኝ ሲሆን በ1996/97 ዓ.ም ከነበረበት 36 ከመቶ በ2006/07 40.8 ከመቶ ሊደርስ ችሏል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በተፈጠረው የትምህርት፣ የሪል-እስቴት፣ የኪራይ እና የንግድ እንቅስቃሴዎች፣ በጅምላና ችርቻሮ ንግድ፣ እንዲሁም የሆቴልና ሬስቶራንት ንኡስ-ዘርፎች እድገት ምክንያት ነው፡፡ በአለፉት አምስት አመታትም ዘርፉ 12.6 ከመቶ፣  10.2 ከመቶ፣ 11.3 ከመቶ፣ 13.7 ከመቶ በቅደም ተከተል አመታዊ አማከኝ እድገት አስመዝግቡአል፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
ፖ ሳ ቁጥር: 1364/530
ስልክ ቁጥር: +251-115-52-81-13
:+251-115-52-81-92
ፋክስ : +251-115-52-20-60
: +251-115-54-25-87
Follow Us
Facebook
google +
youtube
twitter
© 2016 የኢፌድሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት