ዜና ዜና

በኢትዮጵያ ከጥር 2010 እስከ ታህሳስ 2011 ዓ.ም የተረጂው ቁጥር 7.8 ሚሊየን መሆኑ ይፋ ሆነ

የኢትዮጵያ መንግስትና ለጋሽ ድርጅቶች በጋራ ያዘጋጁት ከጥር 2010 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 2011 ዓ.ም ለአንድ አመት ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ቁጥር የሚወስነው የሰብአዊ እርዳታና የአደጋ አይበገሬነት ሰነድ በዛሬው እለት ይፋ አድርገዋል።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር አቶ ምትኩ ካሳ እንደገለፁት በአገራችን በተለይም ከቅርብ አመታት ወዲህ የድርቅ ክስተት እንደቀድሞው በየአስርና በየአምስት አመቱ ሳይሆን ተደጋጋሚነቱን በመጨመር በየአመቱ እየሆነ በኢኮኖሚው እንዲሁም በህዝባችን የአኗኗር ዘይቤ ላይ አሉታዊ ተፅእኖን በማሳረፍ የጎዳን መሆኑን ጠቅሰው የመኸር ወቅት ጥናት ውጤትን መሰረት በማድረግ በሰብአዊ እርዳታና የአደጋ አይበገሬነት ሰነድ ላይ የተመላከተውን በቀጣይ በአገራችን ከጥር 2010 እስከ ታህሳስ 2010 ዓ.ም የሚኖረው የተረጂ ቁጥር 7,880,446 መሆኑንና ለዚህም 1.4 ቢለሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ ይፋ አድርገዋል።

ከዚህም ጋር በማያያዝ በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ የሚታየው የአየር ንብረት መዛባት በአገራችን ላይ አሉታዊ ተፅኖውን በማሳረፍ በተለይም ከቅርብ አመታት ወዲህ ድግግሞሹን በማፋጠን እያደረሰብን ያለውን ጉዳት በመቋቋምና በመከላከል ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት በወገኖች ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመታደግ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ከህብረተሰቡ እንዲሁም ከለጋሽ ድርጅቶችና አጋሮች ጋር በመሆን ወቅታዊ ምላሽ ከመስጠት ጎን ለጎን በዘላቂ ልማት አደጋውን ለመከላከልና ለመቀነስ የሚያስችሉ ልማታዊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በመኸር ወቅት ጥናት መሰረት በአሁነኑ ወቅት የተለየው የተረጂው ቁጥር 7.8 ሚሊየን መሆኑ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ37 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ለዚህም በመኸር ጥናት የተሸፈኑ የሰብል አብቃይና አርብቶ አደር አካባቢዎች ለተከታታይ አመታት በድርቅ የተጠቁ መሆናቸውና ለማገገም አለመቻላቸው በተወሰኑ ኪስ ቦታዎች የዘነበው ዝናብ በመጠንና በስርጭት በቂ አለመሆኑ በቆሎ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች በአሜሪካ ፎል አርሚ ዎርም የተወሰነ የበቆሎ ማሳ መጎዳትና የምርት መቀነስ መታየቱ በአንዳንድ አካባቢዎች የደረሰው የጎርፍ ክስተት ጉዳት ማስከተሉ እንዲሁም በድንበር አካባቢ በተፈጠሩ ግጭቶች በርካታ ሰዎች በመፈናቀላቸው መሆኑ በምክንያትነት ይጠቀሳል።

በሌላ በኩል ደግሞ የተረጂው ቁጥር በ2009 በጀት አመት የበልግ ጥናት ተለይቶ ከነሀሴ 2009 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 2010 ዓ.ም ድረስ የእለት ደራሽ እርዳታ ሲቀርብለት ከነበረው 8.5 ሚሊየን ተረጂ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በ8.4 በመቶ ቀንሶ ታይቷል ።

ለዚህ የድርቅና ሌሎች ቅፅበታዊ አደጋዎች የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ በመስጠት ለመከላከል እንዲቻል መንግስት ብር 5 ሚሊየን በጀት በመመደብ እንቅስቃሴ ላይ መገኘቱን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ገልጸው ቀደም ሲል የተከሰተውን ድርቅ በመቋቋም ሂደት የሰብአዊ አጋሮች በቅንጅት ይሰሩ እንደነበር ሁሉ አሁንም በወገኖቻችን ላይ የተጋረጠውን የድርቅ ስጋት በመቀልበስ ረገድ ድጋፋቸው እንዳይለይ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ከዚህ በፊት ይወጣ የነበረው የሰብአዊ ፍላጎት ሰነድ በምላሽ ላይ ያተኮረ እንደነበር በአሁኑ ወቅት የተዘጋጀው የሰብአዊ እርዳታና የአደጋ አይበገሬነት እቅድ ሰነድ ይዘት በሶስት ምሰሶዎች ላይ ማለትም መከላከልና ማቅለል ምላሽና ለምላሽ ዝግጁነት እንዲሁም የአቅም ግንባታና ማገገም ተካተውበት የሰብአዊ ድጋፍ ሰነዱ ከምላሽ ድጋፍ ባሻገር በመከላከል በማቅለልና በማገገም እንዲሁም በአቅም ግንባታ ላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚያግዝ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

ይፋ በተደረገው የሰብአዊ ፍላጎት ሰነድ የእለት ደራሽ ምግብ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጤናና ስርዓተ ምግብ ትምህርት እንዲሁም መጠለያ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው ሲሆን ለድርቁ ምላሽ ለመስጠት ከሚያስፈልገው የበጀት ፍላጎት ማለትም ከ1ነጥብ 44 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ 7ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር ለምግብ 6ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ለጤና ለተመጣጠነ ምግብ 3ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ለትምህርት 2ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም 6ነጥብ 9 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ደግሞ ለንፁህ መጠጥ አቅርቦት የሚውል ይሆናል።

በብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስተባባሪነት በመኸር ወቅት ሰብል አብቃይና በአርብቶ አደር አካባቢዎች ድጋፍ የሚየስፈልጋቸውን ዜጎች ለመለየት ለሶስት ሳምንታት በተካሄደው የመኸር ምርት ዳሰሳ ጥናት ከሚመለከታቸው የፌዴራል ሚኒስትር መ/ቤቶች ከክልል ቢሮዎች ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካላት እንዲሁም መንግስታዊ ካልሆኑ አለም አቀፍ ድርጅቶች የተውጣጡ 24 ቡድኖች ተሳትፈዋል።

መጋቢት 4/2010 /የኢፌዲሪ መ/ኮ/ጉ/ፅ/ቤት/