ዜና ዜና

የጅቡቲ ወደብ ከሐምሌ ጀምሮ 24 ሰዓት ለመስራት ማቀዱን አስታወቀ

በኢትዮጵያውያን አምራቾችና አስመጪዎች ጥያቄ መሰረት የጅቡቲ ወደብ አገልግሎቱን ወደ 24 ሰዓት ማሳደጉን ባለስልጣኑ አስታወቀ፡፡

ይህን ያለው የጅቡቲ ወደብ እና ነጻ ክልል ባለስልጣን ሲሆን፥ አገልግሎቱን ለመስጠት ያቀደውም ሙሉ ሳምንት መሆኑን ገልጿል፡፡

አገልግሎቱንም ከፊታችን ሐምሌ ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡

አገልግሎቱ ተግባራዊ ሲሆን በወደቡ የሚገኙት ተርሚናል ኦፕሬተሩና ጉምሩኩ ክፍት እንደሚሆኑ ተልጿል፡፡

ከዚህ ቀደም የወደቡ የጉምሩክ አገልግሎትና የዶክመንቴሽን ስራ በሳምንት ለስድስት ቀናትና በየዕለቱ ለ12 ሰዓታት ብቻ ነበር የሚሰራው ተብሏል፡፡

ይህ ውሳኔ የተሰማው ዛሬ በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ነው ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ አብዛኛው ሸቀጧን የምታስገባው በጅቡቲ ወደብ በኩል መሆኑ ይታወቃል፡፡

ባለፈው ወር ታዲያ በጅቡቲ ጉብኝት ያደረጉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጅቡቲን ወደብ በጋራ በማልማት ኢትዮጵያ የንግድ ባለድርሻ በምትሆንበት ጉዳይ ላይ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር መወያየታቸው ይታወሳል፡፡

አዲስአበባ፣ ሰኔ 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)