ዜና ዜና

“የዘንድሮውን የግንቦት 20 ድል በዓል ስናከብር የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር በማድረስ ተጨማሪ ድሎች ለማስገንዘብ መላው ህዝባችን ሊረባረብ ይገባል”-የኢፌድሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት

የዘንድሮውን የግንቦት 20 ድል በዓል ስናከብር የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር በማድረስ ተጨማሪ ድሎች ለማስገንዘብ መላው ህዝብ እንደወትሮው ሊረባረብ እንደሚገባ የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሚንስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሚንስትር አቶ አህመድ ሽዴ ዛሬ በጽ/ቤቱ የግንቦት 20 ድል በዓልን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የዘንድሮው የግንቦት 20 ድል በዓል "የላቀ ብሄራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ፣ለላቀ አገራዊ ስኬት" በሚል መሪ ቃል በመላ አገራችን እንዲሁም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሚገኙባቸው የውጭ አገራት ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖቻችን በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ ይከበራል፡፡

አቶ አህመድ ሽዴ እንዳሉት የግንቦት 20 ድል የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብዝሃነትን ያከበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ በከፈሉት መስዋእትነት የተገኘ ውጤት ነው፡፡ይህ ቀን አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንድትገነባ መሰረት የጣለና የአገራችን ዜጎች ማንነታቸው ተከብሮ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመገንባት የሚያስችል ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኙበት እለት ነው፡፡

ህገ መንግስቱ ህዝቦች ፍላጎታቸውንና እምነታቸውን የገለጹበት ፣በአዲስ መንፈስ የጋራ ግንባር ፈጥረው ፣ተከባብረውና ተጋግዘው አብረው ለመኖር ቃል የገቡበት ሰነድ ነው፡፡ይህ ሰነድ አንድ ጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የአገራችን ህዝቦች ቃል የገቡበት ሰነድ ነው ብለዋል ሚንስትሩ፡፡

የግንቦት 20 ድል በዓል የአገሪቱን የወደፊት ተስፋ እንደገና እንዲያንሰራራ በማድረግ እንደ አገር ለመቀጠል ተደቅኖ የነበረውን ስጋትና ሁኔታ የቀየረ ነው፡፡ሁሉንም ህዝቦች የሚያስተባብር አዲስ የፖለቲካ ስርዓት በመገንባት የአገራችንን ህልውና ያስቀጠለ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአብሮነት ታሪካቸው የሚያሳየው ለሰላም፣ለልትና ዴሞክራሲ ብሎም ለአገራዊ አንድነት ያላቸው ጽኑ አቋም ምንግዜም የማይሸረሸር መሆኑ ነው፡፡አሁን ለደረስንበት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን በኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተደረገው መራር ትግልና የተከፈለው መስዋእትነት የሚያሳየውም ይህንን እውነታ ነው፡፡

የግንቦት 20 ድል የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዘላቂ ሰላም ፣ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ፣ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለማረጋገጥ መሰረትና ዋስትና መሆን የቻለ ነው፡፡ይህም የሆነው በሃገራችን ውስጥ ብዝሃነት የተቀበለና ያከበረ አዲስ ህገ መንግስታዊ ስርዓት መፍጠር ስለተቻለ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በኢኮኖሚው ረገድ በአሁኑ ወቅት በአለማችን ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ላይ ከሚገኙ ግንባር ቀደም አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጭምር ምስክርነት የሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡

በሌላ በኩል በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ውስጥ ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች መንግስት በጥሞና በመመልከት ችግሮቹ በዘላቂነት የሚፈቱበትን መሰረታዊ መፍትሄዎች አስቀምጧል፡፡የመፍትሄ እርምጃዎችንም መውሰድ ተጀምሯል ነው ያሉት ሃላፊ ሚንስትሩ በመግለጫቸው፡፡

መላው የአገራችን ህዝቦች የዘንድሮውን ግንቦት 20 በምናከብርበት ወቅት ዛሬ ላይ ቆመን የወደፊቱን ተስፋ እውን የምናደርግበት እንደመሆኑ መጠን በአገር ግንባታ ሂደት የሁላችንም ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ በዚሁ አጋጣሚ ህዝቡ ከመንግስት ጎን እንዲቀም ጥሪያቸውን አስተላልፍዋል፡፡

ግንቦት 9/2010/የኢፌድሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት