ዜና ዜና

በአገር አቀፍ ደረጃ ግንቦት 19 በሚካሄደው የህዳሴ ግድብ ሩጫ ህብረተሰቡ በመሳተፍ አጋርነቱን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ለማሰባሰብ ታስቦ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ሩጫ ህብረተሰቡ በመሳተፍ አጋርነቱን እንዲያጠናክር ተጠየቀ፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ እንደገለጹት ''ስለ አባይ እሮጣለሁ'' በሚል መርህ በአገር አቀፍ ደረጃ የሩጫ ፕሮግራም ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

የታላቁ ሩጫ ፕሮግራም በሁሉም ክልሎች ግንቦት 19 ቀን 2010 እንደሚካሄድ ገልፀዋል።

ለሩጫው ከተዘጋጀው ካናቴራ ሽያጭ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡

ሩጫው ከገቢ ማሰባሰብ ባሻገር ህብረተሰቡ ግድቡን የሁልጊዜ አጀንዳ አድርጎ እንዲንቀሳቀስ አላማ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፈጠረው ብሄራዊ መግባባት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የማድረግ አላማ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች፣ ኮሌጆችና ሲቪክ ማህበራት እንዲሁም መላው ህብረተሰብ በሩጫው በመሳተፍ አጋርነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅም ህብረተሰቡ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ወይዘሮ ሮማን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ግንቦት 9/2010 /ኢዜአ/