ዜና ዜና

ኢትዮጵያ 12ኛውን የአለም ቻምበርስ ፌዴሬሽን ጉባኤ የማስተናገድ አቅም እንዳላት ገለጸች

ኢትዮጵያ 12ኛውን የአለም ቻምበር ፌዴሬሽን ጉባኤ የማስተናገድ አቅም እንዳላት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አስታወቁ።

ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የዓለም ቻምበር ፌዴሬሽን ዳይሬክተር አንቶኒ ፓርከስን በብሔራዊ ቤተ መንግስት ተቀብለው አነጋግረዋል።

ፌዴሬሽኑ በየሁለት ዓመቱ ጉባኤውን የሚያካሄድ ሲሆን፤ የዘንድሮውን ጉባኤ ለማስተናገድ ከአፍሪካ ኢትዮጵያና ኬንያ፤ ከመካከለኛው ምስራቅ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችና ኢራን በአጠቃላይ አራት አገራት በመፎካከር ላይ ይገኛሉ።

ሆቴል፣ አየር መንገድና የስብሰባ አዳራሽን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የፀጥታ ሁኔታና የአገራቱ መንግስት ቁርጠኝነት ፌዴሬሽኑ የጉባኤውን አስተናጋጅ አገር የሚመርጥባቸው መስፈርቶች ናቸው።

የዘንድሮውን ጉባኤ ለማስተናገድ ሲፎካከሩ ከነበሩ አገራት መካከል ባህሬንና ኦማን ከውድድር ውጭ ሆነዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የኢትዮጵያ ንግድና ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለማዘጋጀት በቂ አቅም እንዳላትና መንግስትም ይህን ለማስፈጸም ዝግጁ መሆኑን ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

የአለም ቻምበርስ ፌዴሬሽን ዳይሬክተር አንቶነየ ፓርከስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ጉባኤውን ማዘጋጀት የሚያስችል መሰረተ ልማት እንዳላትና የኢትዮጵያ የንግድና ማህበራት ምክር ቤትም ከመንግስት ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካለው መዳረሻ አንጻር ከየትኛውም የዓለም ጥግ ወደ አዲስ አበባ በቀላሉ መግባት እንዲቻል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አድንቀዋል።

በአየር መንገዱ አቅራቢያ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች መኖራቸው፣ጉባኤውን ለሚታደሙ እስከ 3 ሺህ አባላት የሚያስተናግድ በቂ አዳራሽ እንዳለ መታዘባቸውንም አክለዋል።

ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት ይህ ጉባኤ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን ለማስተዋወቅና ልምዶችን ለመለዋወጥ እንደሚጠቅምም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ጉባኤውን ለማስተናገድ የሚደረገው ውድድር እስከ ቀጣይ ሚያዚያ የሚቀጥል ሲሆን ፤ ኢትዮጵያ ከኬኒያ፣ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶችና ኢራን ጋር ብርቱ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅባታል።
ኢዜአ፣ አዲስ አበባ የካቲት 29/2010