ዜና ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ፕሬዚዳንት ኪርና ተቃዋሚያቸው ማቻር አዲስ አበባ ፊት ለፊት እንዲገናኙ ጋበዙ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቃዋሚያቸው ሪክ ማቻር አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው ፊት ለፊት እንዲወያዩ ግብዣ ላኩ።

ተቃዋሚው የኤስ.ፒ.ኤል.ኤም ቡድን ባወጣው መግለጫ ለመሪያቸው ሪክ ማቻር የፊታችን ሰኔ 13 2010 በኢጋድ መሪነት ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የፊት ለፊት ውይይት የግብዣ ደብዳቤ እንደደረሰ አረጋግጧል።

የኤስ.ፒ.ኤል.ኤም የኢንፎርሜሽንና የህዝብ ግንኙነት ብሄራዊ ኮሚቴ ሀላፊ ማቦይር ግራንድ ዴ ማቦይር፥ ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር ለሚደረገው የፊት ለፊት ውይይት ግብዣን ፓርቲያቸው እንደተቀበለው አስታውቀዋል።

ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማስፈን ወቅታዊ እና ወሳኝ ደረጃ ላይ መድረሱን እንደሚያደንቁም ገልፀዋል።

ስለ ጥሪው ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በኩል እስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም፤ ለፕሬዚዳንቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ግን የግብዣ ደብዳቤው ለፕሬዚዳንቱ እንደደረሰ እና መቀበላቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ተቃዋሚያቸው ሪክ ማቻር ያቀረቡት ጥሪ ከዚህ ቀደም የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ካቀረቡት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነም ተነግሯል።

ካርቱም ለደቡብ ሱዳኑ መሪ እና ታቃዋሚ ባቀረበችው ጥሪ ላይም በፊት ለፊት ውይይቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደሚገኙም አስታውቃ ነበር።

ኢጋድ ባሳለፍነው ግንቦት ወር በአዲስ አበባ ባካሄደው ስብሰባ ሳልቫ ኪር እና ሪክ ማክቻር ፊት ለፊት ተገናኝተው እንዲወያዩ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

የኢጋድን ጥሪ ተከትሎም የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከረጅም ጊዜ የፓለቲካ ተቀናቃኛቸው እና የአማፂ ቡድን መሪ ሪክ ማቻር ጋር የሰላም ድርድር ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

የደቡብ ሱዳን የአማፂ ቡድን መሪ ሪክ ማቻር በአሁን ወቅት በደቡብ አፍሪካ በቁም እስር እንደሚገኙ ይታወቃል።

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)