ዜና ዜና

ሀገራዊ አንድነት ብሄራዊ ማንነትና ላይ ትኩረቱን ያደረገ ህዝባዊ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

ሀገራዊ አንድነት  ብሄራዊ ማንነት እና ላይ ትኩረቱን ያደረገ ህዝባዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

መድረኩ በብሄራዊ ማንነት እና ሀገራዊ አንድነት ዙሪያ እንዲሁም በታሪክ አጋጣሚ የተፈጸሙ በደሎችና የተዛቡ ታሪኮችን ለማረም የሚረዱ ምክረ ሀሳቦችም ቀርበው ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፥ የሀገሪቱ ህገ መንግስት የዜጎችን የብሄር እና የማንነት ጥያቄ የሚመልስ ነው ብለዋል።

ዜጎች በሚወክሏቸው እና በሚመርጧቸው ግለሰቦች አማካኝነት መተዳደር የሚያስችላቸውን ህገ መንግስታዊ መብት ያገኙበት ነውም ብለዋል በንግግራቸው።

እንጂ አሁን ላይ ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ አዲሱ ትውለድ በአንድነት ላይ የተመሰረተ ልዩነትን አክብሮ ለብሄራዊ አንድነት እና መግባባት የሚጥር ዜጋ ማፍራት ላይ ብዙም እንዳልተሰራበት እና ጊዜው ራሱ ግድ የሚለው መሆኑን አንስተዋል።

ቀጥሎም በውይይት መድረኩ ሁለት የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በቀዳሚው ጽሁፍም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርአት ያመጣቸው ለውጦች፣ መልካም አጋጣሚዎች እና የተጋረጡበት ፈተናዎች በሚል ጉዳይ ላይ ያጠነጠነ ነው።

በዚህ ጽሁፍም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እና ብሄራዊ መዝሙር፤ ብሄራዊ ማንነት እና ሀገራዊ አንድነት ከመገንባት አንፃር ለአብነት ተነስቷል።

በዚህም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እና ብሄራዊ መዝሙር ብሄራዊ ማንነት እና ሀገራዊ አንድነት ከመገንባት አንፃር የተቃኙ መሆናቸው በመድረኩ ተነስቷል።

በዚህ ጽሁፍ ላይ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ሁለት ዋና ዋና ከተሞች ቢኖሩ፤ እንዲሁም ሁለት ወይም ሶስት የሀገሪቱ ቋንቋዎች በሀገሪቱ ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ቢሰጡ መልካም መሆኑን የሚያሳይ ምክረ ሀሳብም ተነስቷል።

በአሁኑ ሰዓትም የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በቀረበው ጽሁፍ ላይ ሀሳብ እና አስተያየት እየሰጡ ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።

 

 አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)