ዜና ዜና

የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት የልዩነት ሃሳቦችን ወደ አንድ ማምጣት ችሏል - የተመድ የልማት ፕሮግራም

የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት የልዩነት ሃሳቦችን ወደ አንድ በማምጣት ረገድ ብዙ ርቀት መጓዙን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የልማት ፕሮግራም አስታወቀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ከተመድ የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በብሄራዊ ማንነትና አገራዊ አንድነት ላይ የሚመክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮችና አገር አቀፍ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በመድረኩ እየተሳተፉ ነው።
የተመድ የልማት ፕሮግራም ተወካይ አሁና ኢዚኮኖዋ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ የተገነባው የፌዴራል ስርዓት የልዩነት ሃሳቦችን በማስተናገድ ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዟል።
በፌዴራል ስርዓቱ የሚታዩ ችግሮችን በግልጽ ተወያይቶ የመፍታት ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ አስገንዝበዋል።

ሁሉም የኅብረተሰብ ተወካዮች በአገር ግንባታ ስራ በሚታዩ ችግሮች ላይ ተወያይተው የጋራ አቋም እንዲይዙ የሚያስችል መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
የተመድ የልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩ መርሀ ግብሮችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሙፈሪሀት ካሚል በበኩላቸው ብሄራዊ ማንነት ከአገራዊ አንድነት ተጣምሮ እንዲሄድ ሁሉም ዜጋ በኃላፊነት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምና አገራዊ አንድነት ላይ የሚያተኩሩ ጥናታዊ ፅሁፎች በመድረኩ ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው በስፍራው የተገኘው ሪፖርተራችን ገልጿል።

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 (ኢዜአ)