ዜና ዜና

የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራጭ የኃይል አቅርቦት ልማት የመሰማራት ፍላጎት አላቸው

በኢትዮጵያ በተለያየ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በአማራጭ የኃይል አቅርቦት ልማት የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተገለጸ።

የኢትዮጵያና የሳዑዲ አረቢያ አምስተኛው የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

የእርሻና የተፈጥሮ ኃብት ሚኒስትር ዴኤታ ካባ ኡርጌሳ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የሁለቱ አገሮች የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ከተቋቋመ በኋላ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ተጠናክሯል።

የሳዑዲ አረቢያ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ መሰማራታቸውን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው ባለሃብቶቹ አሁን ደግሞ በአማራጭ የኃይል አቅርቦት ልማት ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በርካታ የተፈጥሮ ኃብትና አዋጪ የኃይል አቅርቦት ያላት በመሆኑ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ አስረድተዋል። 

በኢትዮጵያና በሳዑዲ አረቢያ መንግስታት መካከል በተለያዩ የትብብር መስኮች የተደረሱ ሥምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። 

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ስብሰባ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ ሰፋ ያለ ውይይት ከማካሄድ ጎን ለጎን በተለያዩ የትብብር መስኮች በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ አዳዲስ የመግባቢያ ስምምነቶችን ይፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሁለቱ አገሮች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ይፋዊ ጉብኝት በማድረግና በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን ያስታወሱት ዶክተር ካባ ሥምምነቶቹን ተግባራዊ ለማድረግ የሁለቱ አገሮች የሥራ ኃላፊዎች የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሳዑዲ አረቢያ የአካባቢ፣ የውኃና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሃማድ ቢን አብዱላዚዝ በበኩላቸው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ግንኙነቱም በተለይም በምጣኔ ኃብት ረገድ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው ሁለቱም አገሮች በጋራ ሊያድጉ የሚችሉባቸው በርካታ እድሎች መኖራቸውንም ነው ያስረዱት።     

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016፤ 1ነጥብ4 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ወደ 659 ሚሊዮን ዶላር ወርዷል።

በተጓዳኝ የሳዑዲ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የሚያካሂዱት የኢንቨስትመንት ሥራ አሁን ላይ 8ነጥብ3 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።

የኢትዮጵያና የሳዑዲ አረቢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሰረተው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1948 ነበር።

ሚያዝያ 8/2010/ኢዜአ