ዜና ዜና

አሜሪካና ኢትዮጵያ በልማትና ጸረ ሽብር ትግል ያላቸውን ትብብር አጠናክረው ይቀጥላሉ

አሜሪካና ኢትዮጵያ በልማት፣ በጸጥታ፣ በሰላምና በጸረ ሽብር ትግል እንዲሁም በኢንቨስትምንት ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋገጡ።

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉበኝት እያደረጉ ያሉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቴለርሰንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሬክስ ቴለርሰን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ጋር ውይይት ከማድረጋቸው ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያው አቻቸው ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር መወያየታቸው ይታወቃል።

ሬክስ ቴለርሰን ከኢትዮጵያ አቻቸው በተጨማሪ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ልቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ጋር ውይይት አድርገዋል።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እንደገለጸው የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሁም ቀጠናዊ ሁኔታዎች ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒትሩና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተወያዩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።

በውይይታቸውም ሁለቱ አገራት በልማት፣ በጸጥታ፣ በሰላምና በጸረ ሽብር ትግል እንዲሁም በኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያረጋገጡ ሲሆን፤ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በጸጥታ ጉዳይ ላይም በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ሬክስ ቴለርሰን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ዳሳለኝ በበኩላቸው የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ያቀረቡበት ዋነኛው ምክንያት የተጀመረው አገራዊ የለውጥ ሪፎርም በፍጥነት እንዲቀጥልና እርሳቸው የመፍትሄ አካል ለመሆን በማሰብ መሆኑን አብራርተዋል።

አዲስ አበባ የካቲት 29/2010(ኢዜአ)