ዜና ዜና

የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ለይፋ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ።

ሰርጌይ ላቭሮቭ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ የኢትዮጵያ አቻቸው ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ከፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ከሌሎች የአገሪቱ መሪዎች ጋር በሁለትዮሽና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ባለፈው ዓመት በሞስኮ ከሩስያ አቻቸው ሴርጌይ ላቭሮቭ ጋር ሽብርተኝነትን በመዋጋት ዙሪያ መወያየታቸው የሚታወስ ነው።

ላቭሮቭ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ የዘንድሮው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን የአሁኑ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል በትምህርት፣ በባህል፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ያለውን ትስስር ዳግም ለማደስ ነው።

ሚኒስትሩ በ2007 ዓም ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ኢትዮጵያና ሩስያ በኃይል ልማት፣ በባቡር መሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር መስማማታቸው ይታወሳል።

የአሜሪካና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዚህ ሳምንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ መምጣታቸው ይታወቃል።

በተለይም ደግሞ የሁለቱ ኃያላን አገራት ሩስያ እና አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በተመሳሳይ ወቅት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው አገሪቱ በዲፕሎማሲው መስክ እያስመዘገበች ያለችው ውጤት ማሳያ መሆኑን ያመላክታል።

አዲስ አበባ የካቲት 29/2010 (ኢዜአ)