ዜና ዜና

በቅርቡ ባወጣው መግለጫ መሠረት የተቀመጡ ተግባራትን የክልሉ መንግስት እንዲሰራ ህዝቡ ጊዜ ሊሰጥ ይገባል

‘‘የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ መሠረት የተቀመጡ ተግባራትን የክልሉ መንግስት እንዲሰራ ህዝቡ ጊዜ ሊሰጥ ይገባል'' ወ/ሮ ኡሚ አባጀማል አባጆርጋ- የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ

ከሠሞኑ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን የንግድ እንቅስቃሴ ማቆምና የመንገድ መዝጋት እንዲሁም የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ኡሚ አባጀማል አባጆርጋ እንዳሉት ከትናንት ጀምሮ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የንግድ ስራ ማቆም፣ መንገድ መዝጋት ብሎም ወደሁከትና ብጥብጥ የሚያመሩ አዝማሚያዎች ታይተዋል።

ቀሪ እስረኞች ይፈቱ የሚልና የልማት ተጠቃሚነትን መነሻ በማድረግ እየቀረበ ያለው የሰሞኑ እንቅስቃሴ አሁን ወደሁከት እየተቀየረ ያለበት ሁኔታ መፈጠሩ በመግለጫው ተገልጿል።

በዚህም በዝዋይ፣ በለገጣፎና በጅማ 8 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በግልና በመንግስት ድርጅቶችና ተሽከርካሪዎች ላይም ጥፋት ደርሷል።

በመግለጫው ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተፈናቅለው በኦሮሚያ አማሬሳ ካምፕ ከተጠለሉ ወገኖች የአራት እንዲሁም በባሌ ዞን መደወላቡ ወረዳ በተፈጠረ ግጭት የሶስት በድምሩ የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተጠቅሷል።

መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት ይህን መሰል ክስተት መፈጠሩ አግባብ አለመሆኑን ያስረዱት ወ/ሮ ኡሚ የክልሉ መንግስት አሁንም አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

መንግስት ጥፋት ያደረሱ አካላት ላይ የማጣራት ስራ በመስራት ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ ሲሆን ህብረተሰቡም በህዝብና በመንግስት መካከል የተጀመረውን የመደማመጥ ሂደት ከሚያደናቅፍ አፍራሽ ድርጊት እንዲታቀብ ጥሪ ተላልፏል።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ ያወጣውን መግለጫ መሰረት አድርጎ ስራዎችን ለመስራት ህዝቡ ጊዜ ሊሰጥ ይገባል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ተጨማሪ ጉዳቶች እንዳይደርሱ የሀይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች የጀመሩትን የማረጋጋት ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

በግጭቱ ሳቢያ ለጠፋው የሰው ህይወት የክልሉ መንግስት የተሰማውን ልባዊ ሀዘን ገልጿል።

የካቲት 6/2010 /የኢፌዲሪ መ/ኮ/ጉ/ፅ/ቤት/