ዜና ዜና

የአፍሪካ ቀንድ አሸባሪነትን ለመዋጋት የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች

በኩዌት እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የፀረ አይ ኤስ ኤስ ጥምረት፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ አሸባሪነትን ለመዋጋት የአለም ዓቀፍ ማህበረሰቡ የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርባለች፡፡

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የአለምዓቀፍ የሽብር ጥቃት እንደደረሰባት በማስታወስ በአለም ዓቀፍ የሽብር እንቅስቃሴ ላይ የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሊቢያ ላይ በንጹኃን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋ እንደማይረሳ በመጠቆም ኢትዮጵያ ለዚህ እኩይ ተግባር ከአለም አቀፉ ማህበረሰቡ ጋር በመሆን አሸባሪነትን እንደምትዋጋ ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ አሸባሪነት በየትኛውም መንገድ ተቀባይነት የለውም ብለዋል ክቡር ሚኒስትሩ ፡፡

ዶ/ር ወርቅነህ እንደገለፁት ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ቁርጠኛ መሆኗንና ለዓለም ሰላምና መረጋጋት ያላትን ታሪካዊ ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች።

አሸባሪ ቡድኑ በመካከለኛው ምስራቅ በተለይም በኢራቅና በሶሪያ ያለው ይዞታ እየተዳከመ ቢመጣም አሁንም በአፍርካና በኤዥያ የተለያዩ አካባቢዎች ይዞታዎች እንዳሉት ገልፀዋል።

ስብሰባው በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የሽብር ተግባር ለመዋጋት የአለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የጋራ መግባባት የደረሰበት ነው፡፡

በስብሰባው የአለም ዓቀፍ ሽብርተኝነት ያለበት ሁኔታ የተገመገመ ሲሆን የጋራ ስትራቴጂም መነደፉን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተገኘው ዘገባ ያመለክታል።

የካቲት6/2010