ዜና ዜና

የቻይና የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ኢትዮጵያን የአፍሪካ አምራች መናኸሪያ አድርጓታል

ቻይና በኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ኢንቨስትመንት አገሪቷን የአፍሪካ አምራች ዘርፍ መናኸሪያ እንዳደረጋትና ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ እንደረዳት በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ገለጹ።

 

አምባሳደሩ ቻይና በኢትዮጵያ እያደረገችው ባለው ኢንቨስትመንት ዙሪያ ከአገሪቷ ዕለታዊ ጋዜጣ ቻይና ዴይሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ከተሾሙ ሁለት ወራት ያስቆጠሩት አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ "አፍሪካ በፍጥነት እየተለወጠች ነው ቻይና በአህጉሩ ያላት ተሳትፎም መልካም ነው" ይላሉ። 

አገሪቷ በኢትዮጵያ የአምራች ዘርፍ እያፈሰሰችው ያለው መዋዕለ ንዋይ አገራቱን ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና ቻይና የትብብር ሞዴል ማሳያ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የኢንዱስትሪ ዞኖች ሲሆኑ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ሶስት የቻይና ኢንዱስትሪ ዞኖች የሚገኙ ሲሆን በአገራቱ መንግስታት ግንባታቸው የተከናወኑ 15 የኢንዱስትሪ ዞኖች ይገኛሉ።

አገራቱ ካላቸው ትብብር አንጻር "የኢንዱስትሪ ዞኖቹ ቁጥር በቂ አይደለም ከዚህ የተሻለ ስራ መሰራት አለበት በዚህ ረገድም ከቻይና ጋር በቅርበት እየሰራን" ብለዋል አምባሳደር ብርሃነ።

በአዲስ አበባ አቅራቢያ የሚገኘው የምስራቅ ኢንዱስትሪ ዞን ከ20 በላይ የቻይና ኩባንያዎችን ቀልብ የሳበ ሲሆን በጫማ ምርት የተሰማራው ሁዋጂያን ዓለም አቀፍ ጫማ አምራች ኩባንያ ይጠቀሳል።

ኩባንያው 1 ሺህ 500 ኢትዮጵያዊያንና 300 ቻይናዊያን ቀጥሮ በመስራትና የሴት ጫማዎችን በማምረት ወደ አውሮፓና አሜሪካ ይልካል።

ከህንድ፣ ቱርክ፣ ብራዚልና ከሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የመጡ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ዞኖች ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ነገር ግን እ.አ.አ በ2015 በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ከተማ ከተካሄደው የኢትዮ-ቻይና የትብብር ፎረም በኋላ በአገሪቷ በኢንዱስትሪ ዞኖች በተለያዩ ምርቶች የተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ይላሉ አምባሳደሩ።

"የቻይና ኩባንያዎች የእኛን ሁኔታ በጥሩ መልኩ ይረዳሉ በመሰረታዊነት በተለይ በልማቱ ዘርፍ አገራቱ ተመሳሳይ ሀሳቦችን ይጋራሉ" ብለዋል አምባሳደር ብርሃነ።

ከሁለት ዓመት በፊት በሀዋሳ ስራውን የጀመረውና በቻይና የሲቪል ምህንድስና ግንባታ ትብብር ተቋም የተገነባው የኢንዱስትሪ ዞን ለ50 ሺህ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠርና በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እቅድ የተያዘበት መሆኑን አስረድተዋል። 

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአምራች ዘርፍ ዋነኛ መዳረሻ ማድረግ እንፈልጋለን በዚህ ረገድ ቻይና በአገሯ ያሉ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማበረታት ድጋፍ እያደረገች ነው ሲሉ አምባሳደሩ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም በቪዛ አሰጣጥ፣ ወደ አገር ውሰጥ የሚገቡ ዕቃዎች በጉምሩክ በኩል ያሉ ጉዳዮችን በፍጥነት በመጨረስና የመሰረተ ልማት አቅርቦችን ተደራሽ የማድረግ ስራ እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት 14 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ከማስመዝገቧ ባለፈ ድህነትን በ55 በመቶ መቀነሷንም አስታውሰዋል።

አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ በቻይና ናንጂንግ፣ ሁዋንግዙና ቾንቺንግ ከተሞች በተዘጋጁ ስብሰባዎች ተሳትፎ በማድረግ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ እንደሰሩ የቻይና ዴይሊ ዘገባ ያመለክታል።

ጥር 7/2010፤ኢዜአ