ዜና ዜና

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ የካቲት 09 ቀን 2010 ዓ.ም

በጠንካራ ህዝባዊ መሠረት ላይ የተገነባው የኢፌዴሪ መንግሥት፣ የተጀመረውን የጥልቅ ተሀድሶ እንቅስቃሴ ከዳር ለማድረስ ተገቢውን ህዝባዊ አመራር መስጠቱን ይቀጥላል!

ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት 26 ዓመታት፣ በኢፌዴሪ መንግሥት እየተመራች ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ የሆነበት መሠረተ ሰፊ፣ ፈጣንና ተከታታይ እድገት በማስመዝገቧ ለዘመናት የዘለቀው አሉታዊ ገጽታዋ ተቀይሯል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዓለም ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ በጣት ከሚቆጠሩ ሀገራት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆናለች። በመሆኑም ሀገራችን የውጭ ኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ እየሆነች መጥታለች።
ሆኖም፣ የተመዘገበው ዙሪያ መለስ ዕድገት አልጋ በአልጋ ሆኖ አልተፈፀመም፡፡ በዚሁ ሂደት፣ በተለይም ደግሞ ከ2007 ዓ.ም. ወዲህ፣ ሕዝቦቻችንን ለምሬት የዳረጉ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባራት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር እጦት የወለዳቸው መጠነ ሰፊ ችግሮች አጋጥመውናል፡፡

ይሁን እንጂ፣ ምንጊዜም ቢሆን አለቃው፣ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብቻ መሆናቸውን በጽኑ የሚያምነው የኢፌዴሪ መንግሥት፣ በሀገሪቱ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ባህሪይና ምንጭ በአግባቡ ለይቶ፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ በተለይ ደግሞ ወጣቶች በየጊዜው ያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ የችግሮችን ስፋት፣ ጥልቀትና ባህሪያት በአግባቡ በመለየት በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የሚፈቱበትን መሰረታዊ አቅጣጫዎች አስቀምጦ የለውጥ ሥራውን ተያይዞታል፡፡ 
በአጭር ጊዜ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል፣ ማለትም የሩቁን ትተን የቅርቡን እንደ አብነት ብናነሳ፣ በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት ጉዳያቸው በክስ ሂደት ላይ የነበሩ እና የተለያዩ ቅጣቶች ተፈርዶባቸው የነበሩ የህግ ታራሚዎች፣ በሀገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሂደት ጥልቀት እንዲኖረውና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲባል ክሳቸው እንዲቋረጥና በይቅርታ እንዲለቀቁ መደረጉ አንዱ ተጠቃሽ ተግባር ነው።

ነገር ግን፣ ሁሉንም ችግሮች በአንድ ጀምበር መፍታት ስለማይቻል በአሁኑ ወቅትም እዚህም እዚያም የፀጥታ መደፍረስና የሰላም መናጋት ሁኔታ እያጋጠመ ይገኛል። ሆኖም ይህ ጊዜያዊ ችግር መንግሥትና ህዝብ እጅ ለእጅ ተያይዘው በአጭር ጊዜ እንደሚፈቱት አያጠራጥርም።

ሆኖም ጥቂት ወጣቶቻችን ማንኛውንም እርምጃ ሲወስዱ፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ተላብሰው በሰከነ አእምሮ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ያስቀመጣቸውን አሠራሮችና የፀደቁ ህጎች አክብረውና አስከብረው እንዲሁም የራሳቸውንና የአገራቸውን ጥቅምና ጉዳት መዝነው ሊሆን ይገባዋል፡፡ ክቡር የሆነውን የሰው ህይወት በከንቱ በመቅጠፍ፣ ሀገሪቱ በሌላት ሀብት የተገነቡ የልማት ተቋማትን በማውደም ችግሮችን መፍታት እንደማይቻልም ሊታመንበት ይገባል፡፡

በተለይም፣ ከእያንዳንዱ ቤተሰብ ወይም ከእያንዳንዱ ኪስ በግብር መልክ በተሰባሰበ ገንዘብ፣ በብዙ ዓመታት ልፋትና ጥረት የተገነቡ መሠረተ ልማቶችንና የህዝብ መገልገያ ተቋማትን፣ የመንግሥትና የግል ንብረቶችን ማውደም፣ የትኛውንም የህዝብ ጥያቄ ሊመልስ የማይችል መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ይልቁንም እየተደረገ ያለው አፍራሽ እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ፣ በዋነኛነትም ወጣቱ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ጠልፈው ሌላ ድብቅ ዓላማቸውን ለማራመድ የሚፈልጉትን የውስጥና የውጭ ኃይሎች አፍራሽ ዓላማ ያሳካ እንደሆነ እንጂ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም አንዳችም ፋይዳ የለውም፡፡

ስለሆነም፣ ከየትኛውም የሀገሪቱ አቅጣጫ የሚነሱ አውዳሚ ተግባራትን ሁሉ ከማንም በላይ የመከላከል ኃላፊነት ያለባቸው የነገዋ አገር ተረካቢ ወጣቶች መሆናቸውን በውል ተገንዝብው ሀገራቸውና ህዝባቸውን በሚጠቅም በጎ ተግባር ላይ ሊያተኩሩ ይገባል፡፡ 
የኢፌዴሪ መንግሥት፣ የህዝቡን ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ለመመለስ ጠንክሮ እየሠራ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀው እና ትልቅ ትርጉም ያለው ተግባርም ተፈጽሟል። ይኸውም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ነው፡፡

እንደሚታወቀው፣ ከግንቦት 20/1983 ዓ.ም. በፊት በነበረችው ኢትዮጵያ የመንግሥት በትረ ሥልጣን በጠመንጃ አፈሙዝ አሊያም በሞት ካልሆነ በስተቀር ወደሌላ ሰው በማይተላለፍባት አገር ላይ ይህን መሰሉ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ጥያቄ መቅረቡ በራሱ የአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ አመላካች ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ በአጋጣሚ የሆነ ነገር አይደለም። ይልቁንም በኢፌዴሪ መንግሥት መርሆዎችና እሴቶች ሲቃኝ ሥልጣን በግለሰቦች እጅ የሚቆይ ርስት ሳይሆን መነሻውም ሆነ መድረሻው የህዝብ ማገልገያ ነው ከሚል ተራማጅና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እና ጽኑ እምነት የመነጨ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡ የኢፌዴሪ መንግሥት ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ያደረገው ይህ ገዥ አስተሳሰብ በቀጣዩ ጉዞም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህል ሆኖ እንደሚቀጥል የኢፌዴሪ መንግሥት ያረጋግጣል፡፡

የተጀመረው የዳግም የጥልቅ ተሃድሶ ዋንኛው ሞተርና ባለቤት ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተገቢውን አመራር ለመስጠት እንዲቻልም፣ የኢፌዴሪ መንግሥትን እየመራ ያለው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ራሳቸውን በጥልቀት ገምግመው ያስቀመጧቸውን መሰረታዊ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች መሬት ላይ ለማስነካት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ያጠናቀቁበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
በአጠቃላይ፣ የለውጡ ባለቤት የሆነው ምልዓተ ሕዝቡ እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም፣ ነገም ከኢፌዴሪ መንግሥት ጎን ተሰልፎ ስለሚረባረብ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ የሚገታው አንዳችም ሀይል አይኖርም። የሀገሪቱ ፈጣን ዕድገትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አያጠራጥርም።

በአጭሩ፣ አሁን የምንገኝበት ወቅት በሀገራችን የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞን ከዳር ለማድረስ የምንረባረብበት ምዕራፍ ነው። የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች፣ የኢፌዴሪ መንግሥት ብቻውን በሚያደርገው ሩጫ እንደማይመለሱ ተሰምሮበት ያደረ ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም የሲቪክ ማህበራት፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የተለያዩ ህዝባዊና የሙያ ማህበራት፣ በአጠቃላይ ምልአተ ህዝቡ የተጀመረው የጥልቅ ተሀድሶ ዳር እንዲደርስ አስፈላጊውን ርብርብ እንዲያደርጉ የኢፌዴሪ መንግሥት በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በዚህ አጋጣሚ፣ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከመንግሥት ጎን ቆመው የጥልቅ ተሀድሶ እንቅስቃሴውን ከዳር ለማድረስ የድርሻቸውን በመወጣት ላበረከቱት ዙሪያ መለስ ተሳትፎ የኢፌዴሪ መንግሥት ለመላው ህዝባችን ምሥጋናውን ያቀርባል፡፡

የህዝብ ይሁንታ አግኝቶ በጠንካራ ህዝባዊ መሰረት ላይ የተገነባው የኢፌዴሪ መንግሥትም የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ከዳር ለማድረስ ተገቢውን ህዝባዊ አመራር መስጠቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ያረጋግጣል።