ዜና ዜና

ህዝቡ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እየሰራ በመሆኑ በርካታ ለውጦች ማምጣት ተችሏል-የኮማንድ ፖስት ዋና ሴክሬታሪያት

ህዝቡ ሰላሙና መደበኛ የኑሮ እንቅስቃሴው እንዳይስተጓጎል ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ተባብሮ በመስራት የሁከትና ብጥብጥ ሀይሎችን ለመመከት ከኮማንድ ፖስት የጸጥታ ሃይሎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እየሰራ በመሆኑ በርካታ ለውጦችን ማምጣቱን የኮማንድ ፖስቱ ዋና ሴክሬታሪያትና የመከላከያ ሚኒስትር ክቡር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ገለጹ።

ሚንስትሩ ይህን ያሉት በጽ/ቤታቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ጊዜ ጀምሮ በነበረው ሂደት ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶች አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ነው፡፡

አቶ ሲራጅ እንዳሉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የፌዴራል ኮማንድ ፖስት የራሱን ዝርዝር እቅድና የአፈጻጸም መመሪያ አውጥቶ በተዋረድ በቀጠና በመከፋፈል ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል፡፡

ህዝቡ ሰላሙንና መደበኛ የኑሮ እንቅስቃሴው እንደይስተጓጎል ከከኮማንድ ፖስት የጸጥታ ሃይሎች ጋር ተባብሮ በመስራት የሁከትና ብጥብጥ ሀይሎችን ለመመከት እንዲችል ከኮማንድ ፖስቱ ጋር ውይይት አድርጓል ያሉት አቶ ሲራጅ ሁሉም የጸጥታ አካላት በአንድ የኮማንድ ፖስት ስር ሆነው በየቀጠናው የተቋቋሙት ኮማንድ ፖስቶች በየአካባቢው ያሉትን የጸጥታ አካላት በሙሉ አንድ እቅድ አውጥተው ሁሉንም በማሰባሰብ በጋራ ተወያይተው የጋራ አቋም ይዘው በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ ነው ያሉት በመግለጫቸው፡፡

ይህ በመሆኑም በአድማ ምክንያት ተዘግተው የቆዩ መንገዶች ወደ ቀድሞ አገልግሎታቸው መመለሳቸውን ጠቁመው ያልተከፈቱ ጥቂት መንገዶችን በፍጥነት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል በቂ የጸጥታ ኃይልና ተንቀሳቃሽ ጥበቃ ተመድቧል ነው ያሉት ሚንስትሩ፡፡

አክለውም የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት የማይፈልጉ ኃይሎች የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ እንዳይሆን በርካታ የሁከትና የአድማ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መቀየታቸውንም አንስተዋል፡፡

"የታወጀው አዋጅ ወደ መሬት እንዳይወርድ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። አገር አቀፍ የስራ ማቆም አድማ በተለያዩ አግባብ ቅስቀሳ ተካሄዷል። የህዝብ ትራንስፖርት፣ ረጃጅም ትራንስፖርቶች ላይ የሚጓጓዙትን ጭምር በተገቢው እንዳይሄዱና እንዲደናቀፉ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። ዜጎች ከቦታ ቦታ በሰላማዊ መንገድ እንዳይቀሳቀሱ መንገዶችን በተለያዩ አግባብ፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ግንዲላ በማጋደም፤ አንዳንድ ቦታ ላይ ድንጋዮችን በመከመር፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመኪኖቹን ቁልፍ ጭምር በመቀማት በዚህ መልክ የነውጥ ኃይሎች ሁከት በመፍጠር ሰላማዊ የዜጎች እንቅስቃሴ እንዳይፈጠር በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል።"

የተለያዩ መሳሪያዎችን በመጠቀም "ወደ 17 የጸጥታ አካላት የመቁሰልና ለጉዳት ተዳርገዋል፣በተደራጀ ነውጥ የጸጥታ አካላትንም ጭምር በመተናኮስ ለምሳሌ ቦምብ በመወርወር፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ሳይቀር ቦምብ በመወርወር፣ የፖሊስ አካላት እንዲቆስሉና ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረግ ችለዋል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ በዱላ፣ በጩቤ፣ በገጀራ፣ በተለያየ መልክ እየታገዙ የጸጥታ አካላት ላይ ጥቃት ለመፈጸም ጥረት አድርገዋል።"

መንግስት እንደዚህ አይነት አለመረጋጋቶችን ቀልብሶ የዜጎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ የመመለስ ግዴታ አለበት ለዚህም የኮማንድ ፖስቱ በቅንጅት እየሰሩ ይገኛል ነው ያሉት ፡፡

ሰላም በማስከበሩ ሂደት ያልተመጣጠነ እርምጃ የወሰደ የጸጥታ አካል ካለ ተጣርቶ በህጋዊ አግባብ ተጠያቂ የሚሆንበትን ስርዓት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስቀመጡንም ገልጸዋል።

የሁከትና ብጥብጥ ሀይሎች ዋናው ፍላጎታቸው መንግስት ገምግሞ ያስቀመጣቸውን የመልካም አስተዳደር፤የልማት ክፍተቶችን በመጠቀምና ወደራሳቸው አጀንዳ በመውሰድ እንደሽፋን በመጠቀም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ህገወጥ በሆነ መንገድ ለማፍረስና የስልጣን ፍላጎታቸውን በአቋራጭ ለማግኘት እንዲሁም የህግ የበላይነት እንዳይሰፍንና የህግ የበላይነት ላይ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ማድረግ ነው ብለዋል አቶ ሲራጅ፡፡

የህዝቡ ትክክለኛ ጥያቄዎች አሉ፤እነዚህን ጥያቄዎች መንግስት እቅድ አውጥቶ ተቀብሎ ለመፍታት እየሰራ ነው ያሉት ሚንስትሩ ህዝቡ በፍጥነት እንዲመለሱ የጠየቃቸውን እነዚህን ጥያቄዎች መንግስት ከህዝቡ ጋር ባንድ ላይ ለመፍታት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ህዝቡም ሰላም ተረጋግጦ መንግስት ልማቱን፤ሰላሙን ፤የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና መመለስ ያለባቸውን ጥያቄዎች ባግባቡ እንዲመለሱ ይሰራልም ብለዋል፡፡

መንግስት ይህን እየሰራ ባለበትና በኢኮኖሚው ፣በማህበራዊ ልማቶች፣በመሰረተ ልማት፣በግብርናው ዘርፍ ፣በኢንዱስትሪው መስክ፤ በከተማ ልማቱና በሌሎችም ለውጥ እያስመዘገበ ባለበት ጊዜ ወጣቶችና ህጻናት ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለሚያራምዱ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ህብረተሰቡ በተለይም ቤተሰብ አበክሮ ሊሰራ እንደሚገባ አቶ ሲራጅ ጥሪ አቅርበዋል።

የካቲት 28/2010/የኢፌዴሪ መ/ኮ/ጉ/ጽ/ቤት