ዜና ዜና

የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለ እድሜ ጋብቻ ለማስወገድ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለ እድሜ ጋብቻ ለማስወገድ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን የሴቶች እና ህፃናት ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም ደረጃ ለ107 ሀገር አቀፍ ለ42ተኛ ጊዜ "በተደራጀ የሴቶች ተሳትፎ እና ንቅናቄ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን እናረጋግጣለን" በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የሴቶች እና ህፃናት ጉዳዮች ሚንስትሯ ወ/ሮ ደሚቱ ሀምቢሳ ቀኑ ሴቶች ካለባቸው ውስብስብ ችግር ተላቀው በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ለማመቻቸት ያግዛል ብለዋል፡፡

ህገ-መንግስቱን መነሻ በማድረግ የቤተሰብና የወንጀል ሕግ እንዲሁም የአሰራር ማእቀፎች ስራ ላይ በመዋላቸው የሴቶችና ህጻናት ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል ወ/ሮ ደሚቱ፡፡

ያም ቢሆን በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ጥቃቶች ሳቢያ የሴቶችን የተጠቃሚነት በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ እንቅፋት እየሆነ መሆኑን ሚንስትሯ አመልክተዋል።

ሴቶች ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊትም ሆነ ከጥቃት ሊጠበቁ የሚችሉት የኢኮኖሚ አቅማቸው ሲጎለብት መሆኑን ሚንስትሯ ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ጐጂ ልማዳዊ ድርጊትን በተለይ ደግሞ የሴት ልጅ ግርዛት እና ያለ እድሜ ጋብቻን በ2017ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቱም ተናግረዋል።

ሚንስትሯ ሠላም የህልውናችን ወሳኝ በመሆኑ ሴቶች ከቤተሰብ መሪነት ጀምሮ በሀገር የሰላም ግንባታ ትልቅ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገም አመልክተዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች አለመግባባቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ ቀዳሚ ተጠቂና የችግሩ መፍትሄ ሴቶች በመሆናቸው በሃገሪቱ አልፎ አልፎ ለሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች ዜጎችን በማስተማር ትልቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው በውይይቱ ተገልጿል፡፡

የካቲት 29፣2010/ኢቢሲ/