ዜና ዜና

ከመደበኛ በታች የበልግ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች እርጥበቱን በአግባቡ ሊጠቀሙ ይገባል

በመጪው በልግ ከመደበኛ በታች ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች የሚገኘውን እርጥበት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው የእርሻና ተፈጥሮ ሐብት ሚኒስቴር አሳሰበ።

ሚኒስቴሩ በ2010 የበልግ ወቅት የአየር ሁኔታ አዝማሚያ ምክረ ሀሳብ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

ብሄራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሚሰጠውን ትንበያ መሰረት በማድረግም አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮችና በግርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ሊያደርጉ ስለሚገቧቸው ቅደመ ዝግጅቶችና ጥንቃቄዎች ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።

የ2010 ዓ.ም በልግ ከየካቲት አጋማሽ እስከ ግንቦት መጨረሻ ያለውን ጊዜ ያካትታል።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አለማየው ብርሃኑ እንደገለጹት በአብዛኛው የበልግ አብቃይ አካባቢዎች የዝናቡ አገባብ ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ መሆኑን የኤጀንሲው ትንበያ ያመለክታል።

ምዕራባዊ የአገሪቱ አካባቢዎች በአብዛኛው ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን ደቡብና ደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

ሰሜንና ማዕከላዊ የአገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ ሲያገኙ፤ ሰሜን ምስራቅ፣ ምስራቅና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቷ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚያገኙ ኤጀንሲው መተንበዩን ተናግረዋል።

እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ በበልግ እርሻ እንቅስቃሴ የተሻለ ምርት ለማግኘት አርሶ አደሩ ምክረ ሀሳቡን ተግባራዊ ማድረግ አለበት።

የበልግ ምርት ለሰሜን፣ ለሰሜን ምስራቅና ለምስራቃዊ ደጋማ አካባቢዎች ከአምስት እስከ 30 በመቶ፣ ለደቡብና ደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ ከ30 እስከ 60 በመቶ ጠቅላላ ዓመታዊ ምርታቸውን ይሸፍናል።

በመሆኑም ከመደበኛ በታች ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች የሚገኘውን እርጥበት በአግባቡ መጠቀም የሚችሉበትን አሰራር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

የሚገኘውን የዝናብ ውሃ ወደ አፈር ውስጥ በማስረግና እንዳይባክን በማድረግ ውጤታማ የውሃ ማሰባሰቢያና ማቆሪያ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

በኩታ ገጠም የሚያመርቱ አርሶ አደሮች የተጎዱ የማሳ ውስጥ እርከኖችን መጠገንና አዲስ መስራት፣ የውሃ ማሰባሰቢያ ቦዮችን መጠቀምና የአፈር እርጥበት እንዳይተን መስራት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

የሚዘሩ ሰብሎች ምግብ እንዳይሻሙ በማድረግ ውጤታማነታቸውን ለማሳደግ በባለሙያ ምክር በመታገዝ በመስመር መዝራት እንደለባቸውም አክለዋል።

''የአነስተኛ መስኖ ሥራዎችን ማስፋፋት ይገባል ያሉት'' አቶ አለማየሁ ይህም በተለያዩ ምክንያቶች ሊቀንስ የሚችለውን ምርት ለማካካስ እንደሚረዳ አብራርተዋል።

መጪው ወቅት ሙቀት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጸረ ሰብል ተባዮችን ማጥፋት ላይም በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

አርሶ አደሩ ተባይ መከሰትና አለመከሰቱን ለመለየት የተጠናከረ አሰሳ ማድረግና በባለሙያዎች የሚሰጠውን ምከረ ሀሳብ መተግበር እንደሚኖርበትም አክለዋል።

በየአካባቢዎቹ ተባይ ለማጥፋት የተዋቀሩ ግብረ ኃይሎችም ተባዮች ሊራቡ የሚችሉባቸውን ቦታዎች መለየትና መከላከል እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል የበልግ እርሻ እንቅስቃሴውን ውጤታማ ለማድረግ ለአርሶ አደሩና ለባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

በቶሎ የሚደርሱና የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ከምርምር ተቋማትና ከዘር አቅራቢ ድርጅቶች ጋር እየተሰራ መሆኑንም አውስተዋል።

አዲስ አበባ የካቲት 27/2010(ኢዜአ)