ዜና ዜና

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቀነስ የሀይማኖት አባቶች ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቀነስ የሀይማኖት አባቶች የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው የዓለም ዓቀፍ የስደተኞች ማህበር ገለፀ።

በህገ-ወጥ ስደትና አዘዋዋሪዎች ላይ ያተኮረ፣ የሀይማኖት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

አለም ዓቀፉ የስደተኞች ማህበር ተወካይ ሚስተር ቬስ ሃቱንጊማና "ችግሩ በሚታይባቸው አካባቢዎች ካሉት የማህበረሰብ አባላት ጋር በቅርበት መስራታችንና የሀይማኖት አባቶች ተሳትፎ ጠንካራ መሆኑ ህብረተሰቡ ህገ-ወጥ ስደት የሚያደርሰውን አስከፊ ጉዳት በተጨባጭ እንዲገነዘብ አስችሎታል" ብለዋል።

በተሰራው ስራ ህብረተሰቡ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚያመጣውን ከባድ አደጋ ከመገንዘቡ ባለፈ በአገር ውስጥ ያሉትን አማራጮቸ እንዲመለከት አስችሎታል በማለት ጥረቱን አድንቀዋል።

በአለም ዓቀፉ የፍልሰት ድርጅት ብሄራዊ የፕሮግራም ኦፊሰር ወይዘሮ ልዩነት ደምስስ፤ የገጠሩ ማህበረሰብ በተለየ ሁኔታ ስለ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር አስከፊነት ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረው፤ "የሀይማኖት አባቶችና ወላጆች ስደቱን ለመቀነስ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል" ብለዋል።

'በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እኤአ በ 2016 በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የወጡት ስደተኞች ቁጥር 20 ሺ እንደነበርና አሁን ላይ ቁጥሩ ወደ 13 ሺ ዝቅ ማለቱንም ጠቅሰዋል።

"የተመዘገበው ለውጥ ችግሩ ግንዛቤ እያገኘ መምጣቱን ያሳያል" ብለዋል።

በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በሱማሌ ክልሎች ህብረተሰቡ ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችንና ደላሎችን በማጋለጡ ባለፉት ሶስት ዓመታት ችግሩን መቀነስ መቻሉን ጠቁመዋል።

የኢትዮዽያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሊቀመንበር ንቡረ እድ ኤልያስ አብረሀ የሀይማኖት ጉባኤው ህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ያለው ግንዛቤ እንዲያድግና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት "የማህበረሰቡ ተሳትፎ እንዲጎለበት እየሰራን ነው" ብለዋል።

ችግሩን ለመቀነስና ለወደፊት መሰራት ያለባቸውን ጉዳዮች ለይቶ በመግባባትና ቃል በመግባት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አማራጭ እንደማይሆን ለማስተማር መድረኩ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት የመጡት ሼህ ዑመር ኢማም ዑመር በበኩላቸው፤ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የህይወት መንገድን የሚያሰናክል በመሆኑ ችግሩን በተመለከተ በቋሚነት ምክር ቤቱ ትምህርት እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

"ራሳችሁን ለአደጋ አታጋልጡ" የሚለውን የሀይማኖት አስተምሮ መሰረት በማድረግ ህብረተሰቡን በማስተማር የተሻለ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።

ከሶስት ዓመታት በፊት ለሀጅ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከሄዱት መካከል ዘጠኝ መቶ የሚሆኑት ሳይመለሱ እንደቀሩ ያስታወሱት ሼህ ኡመር፤ ምክር ቤቱ በሰጠው ትምህርት ዘንድሮ ከሀጅ መንገደኞች መካከል እዚያው የቀሩትን ሰዎች ቁጥር ወደ 30 መቀነስ መቻሉን ጠቅሰዋል።

የካቲት 27/2010 /ኢዜአ/