ዜና ዜና

ኢትዮጵያ ከሶስቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉብኝት ምን ታተርፋለች?

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከነገ ጀምሮ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የአሜሪካ እና ሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሊያካሂዱ መሆኑ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ እያደረገችው ያለውን እንቅስቃሴ ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን አስታውቋል።

ከትላንት ጀምሮ የኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የጋራ የሚኒስትሮች የኮሚሽን ስብሰባ በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ በአዲስ አበባ የጋራ ውይይት እያካሂደ ነው።

ረቡዕ ደግሞ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼህ አብዱላሂ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ የትብብር መስኮች ዙርያ ውይይት ያደርጋሉ።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፥ አሁን ላይ ከ98 በላይ የሚሆኑ የአቡዳቢ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ተሰማርተው ከ10 ቢሊየን ብር በላይ ፈሰሰ አድርገዋል።

በአሁኑ ወቅትም አዲስ አበባ ተጨማሪ የአቡዳቢ ኩባንያዎች በመሰረተ ልማት፣ አርንጓዴ ልማት፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በሃይል ልማት እና በባቡር መስመር ዝርጋታ እንዲሳተፉ ጥረት እያደረገች ነው።

ነገም ሚኒስትሮቹ በሚገኙበት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ እነዚህ ነጥቦች ትልቅ መወያያ ሆነው ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተያያዘ ዜና አዲስ አበባ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተጨማሪ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት ነገ ይጀምራሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ከአውሮፓውያኑ 1903 ጀምሮ በመካከላቸው ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት አላቸው።

ይህም በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ ሰላም እና ደህንነት፣ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፣ በዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዩች በየአመቱ የሚነጋገሩበት መድረኮች እንዳሉ አብራርተዋል።

አዲስ አበባ እና ዋሽንግተን ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈም መረጋጋት በተሳነው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የተደቀነውን የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ለመግታት ጠንካራ ግንኙነት መስርተው እየተንቀሳቀሱ ነው።

በአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስርያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ ትናንት በስክል በሰጡት ማብራርያ፥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት በኢትዮጵያ የመጀመራቸው ዋናው ምክንያት ሀገሪቱ በአህጉሩ ካላት ተሰሚነት አኳያ እና የአፍሪካ ህብረት፣ ሌሎች ክፍለ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ተቋማት መገኛ በመሆኗ ተፅእኖዋ የጎላ በመሆኑ ነው ብለዋል።

አሜሪካ የኢትዮጵያን ማደግ እና መልማት ትሻለች ያሉት አምባሳደር ያማማቶ፥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም የንግድ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ከሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ጋር ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል ነው ያሉት።

ከነገው የሬክስ ቲለርሰን ጉብኝት ማግስት የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ሀሙስ በአዲስ አበባ ጉብኝት ያደርጋሉ።

የኢትዮ ሩስያ የዲፕሎማሲ ግንኙነትም 120 አመታት ያስቆጠረ ነው።

በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ እና ሞስኮ በምጣኔ ሀብት፣ በሳይንስ እና በቴክኒክ ትብብሮች፣ ተደራራቢ ታክስን ማስቀረት የሚችል ስምምነት እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ ስምምነቶችን ተፈራርመወል።

ቃል አቀባዩ የአሁኑ የሰርጌ ላቭሮቭ ጉብኝትም ይበልጠ ይህን ግንኙነት ለማጠናከር ታሳቢ ያደረገ ነው ይላሉ።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከሶስቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙርያ በትብብር እያከናወነችው ያለውን ስራ ማጠናከር የሚያስችላት ውይይት ታደርጋለች ብለዋል።

በዚህም ውይይቶቹ ግንኙነቱን ከማጠናከር በዘለለ በአከባቢው ሰላም እና ደህንነት ላይ የሚመክሩ በመሆናቸው ለኢትዮጵያ ብሎም ለቀጠናው ሀገሮች ያለው ፋይዳ የላቀ ነው።

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 27፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)