ዜና ዜና

የሕዳሴው ችቦ መቀሌ ከተማ መግባቱን ተከትሎ 6 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ እየተሰራ ነው

የሕዳሴው ግድብ ችቦ ዛሬ መቀሌ ከተማ መግባቱን ተከትሎ 6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማሳባሰብ እየተሰራ መሆኑ የከተማው ምክትል ከንቲባ አስታወቁ።

የሕዳሴው ግድብ ችቦ ዛሬ ከትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን ወደ መቀሌ ከተማ ሲገባ በህዝቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

በአቀባበል ስነስርአቱ ላይ ከትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን አስተዳደሪ ችቦውን የተረከቡት የመቀሌ ከተማ ምክትል ከንቲባ ብርሃነ ገብረሊባኖስ ናቸው።

ችቦው ከዛሬ ጀምሮ በከተማዋ በሚቆይባቸው አምስት ቀናት ከከተማው ሕዝብ በቦንድ ግዥና በተለያዩ መንገዶች 6 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።

የመቀሌ ከተማ ህዝብ በአራት ተንቀሳቃሽ ባንኮች ዛሬ ቦንድ መግዛት መጀመሩን ምክትል ከንቲባው ጠቁመው፣ ህዝቡ በትግል ወቅት በህብረት ያሳየውን ጀግንነት በሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲደግም ጥሪ አቅርበዋል።

የትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ገብረሕይወት ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው ችቦው በዞኑ በነበረው የአምስት ቀን ቆይታ 5 ሚሊዮን ብር በቦንድ ግዥ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በቀጣይም የአንድ ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ በተለያዩ መንገዶች ለማሰባሰብ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

የክልሉ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግኑኝነት ኃላፊ አቶ ብርሃነ ተክሉ በበኩላቸው፣ ከየካቲት 1 እስከ 26 ቀን በላው ጊዜ ውስጥ የመቀሌ ከተማን ሳይጨምር ችቦው በተዘዋወረባቸው በስድስት ዞኖች ሕብረተሰቡ 30 ሚሊዮን ብር በቦንድ ግዥ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በዘንድሮው ዓመት በክልሉ በተለያዩ መንገዶች ለመሰብሰብ የታቀደውን 83 ሚሊዮን ብር ገንዘብ ለማሳካት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀስ አንዳለባቸውም አመልክተዋል።

"በትግሉ ወቅት ልጆቻችን የከፈሉት መስዋዕትነት ዋጋ የሚኖሮው በአባይ ሕዳሴ ግድብ ተዋናይ ስንሆን ነው" ያሉት ደግሞ በሁለት ልጆቻቸውና በራሳቸው ሥም የአምስት ሺህ ብር ቦንድ የገዙት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዘብረአብሩክ ደስታ ናቸው።

የትግራይ ሕዝብ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ከ526 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ዋቢ አድርጎ የዘገበው ኢዜአ ነው።
ኢዜአ፣ መቀሌ የካቲት 26/2010