ዜና ዜና

የመኖ ጥራትን በመጠበቅ በወተት ውስጥ መርዛማ ንጥረ ነገር መከላከል እንደሚገባ ተጠቆመ

የእንስሳት መኖ ጥራትን በመጠበቅ በወተት ምርት ላይ የሚከሰተውን አፍላቶክሲን የተባለ መርዛማ ንጥረነገር መከላከል እንደሚገባ የእንስሳትና አሳ ሃብት ሚኒስቴር አሳሰበ።

የወተት ጥራት አጠባበቅና ደህንነትን አስመልክቶ ሁለት ቀን በቢሾፍቱ ከተማ የተካሄደ አውደ ጥናት ዛሬ ተጠናቋል።

የእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ሚኒስትሩ ዶክተር ገብረእግዚአብሔር ገብረዮሐንስ እንደገለፁት ከገበያ የሚገዙ መኖዎች የጥራት መጓደል በወተት ምርት ላይ የአፍላቶክሲን መጠን እንዲጨምር ምክንያት ስለመሆኑ በጥናት ተረጋግጧል።

ጥራቱን የጠበቀ መኖ ለከብቶች በማቅረብ ደህንነቱ የተረጋገጠ የወተት ምርት በማምረት የተጠቃሚውን ጤና መጠበቅ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን አሳስበዋል።

"የእንስሳት አርቢውን አመለካከት፣ እውቀትና ክህሎት ማሻሻል፣ የመኖ አያያዝና ክምችት ስርዓትና የመኖ ማቀነባሪያ ፋብሪካዎችን ዘመናዊ ማድረግ ትኩረት የሚሰጣው ጉዳይ ነው " ብለዋል።

በመንግስት በኩል ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የአሰራር ስርአቶችና የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ መድረኩ  በአገሪቱ የእንስሳት ምርትና ተዋጽኦ ጥራትን የማረጋገጥ ሥራ ለመጀመር በችግሮች፣ መፍትሄዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ የተዘጋጀ ነው።

በወተት ላይ ምርምር ያካሄዱት ዶክተር ርህራሄ መስፍን በበኩላቸው አፍላቶክሲን በእንስስት መኖና በእንስሳት ተዋጽኦ ላይ ያለውን ገጽታ በማስመልከት ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።

ተመራማሪዋ እንዳሉት አፍላቶክሲን በእንስሳት መኖ አቀማመጥ ችግር፣ በሙቀትና እርጥበት ምክንያት የሚከሰትና የመኖ ንጥረ ነገሮችን የሚያበላሽ ነው።

"በአፍላቶክሲን የተበከለ የወተት ምርት መጠቀም ደግሞ የጉበት ካንሰር ያስከትላል" ብለዋል።

የእንስሳት መኖ ልማቱን ለማስፋፋት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ጥራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሚኒስቴሩ የጤናና መኖ ቁጥጥር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ምስራቅ መኮንን በበኩላቸው ጥራት ያላቸውን እንስሳት ማርባት፣ የአረባብ ሥርዓትን እንዲሁም የአመጋገብና የጤና አያያዝን በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ከሁሉም ባለድርሻ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል ።

"በዝርያ ማሻሻል ለሚሳተፉ አርሶና አርብቶ አደሮች የተሻሻለ የመኖ ዝርያ በማቅረብ በጥራት እንዲያለሙና በእርባታው ስኬታማ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል" ያሉት ዶክተር ምስራቅ ለተግባራዊነቱም የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

አዳማ የካቲት 21/2010/ኢዜአ