ዜና ዜና

አርሶ አደሩ የግብርና መካናይዜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት በቅርበት እንዲያገኝ እየተሰራ ነው

አርሶ አደሩ የግብርና መካናይዜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎትን በቅርበት እንዲያገኝ በጥቃቅንና አነስተኛ ማይክሮ ኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ወጣቶች በዘርፉ እንዲሳተፉ በመደረግ ላይ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚንስቴር ገለጸ።

አምስት የወጣቶች ጥቃቅንና አነስተኛ ማይክሮ እንተርፕራይዞች ከሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የግብርና መካናይዜሽን መሳሪያዎች ተበርክቶላቸዋል።

ለወጣቶቹ ከተሰጡት መሳሪያዎች መካከል ከጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ደርጀት በተገኘ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ የተገዙት አምስት የእርሻ ትራክተሮች ይገኙበታል።

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚንስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ መንግስቴ በትራክተሮቹ ርክክብ ወቅት እንዳሉት ማሳሪያዎቹን አርሶ አደሩ የግብርና መካናይዜሽን አገልግሎቱን ከተደራጁ ወጣቶች በስፋትና በቅርበት እንዲያገኝ ለማስቻል ነው።

ወጣቶቹ በአርሲ ዞን በምርታማነታቸው በሚታወቁ አምስት ወረዳዎች በግብርና መካናይዜሽን ኦፕሬተርነት ተደራጅተው ተገቢውን ሙያዊ ዕውቀት በማግኘት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ወጣቶቹ በቀጣይ የማሽነሪ ሊዝ አገልግሎት፣ የብድር፣ የክህሎትና የሙያ ስልጠና ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ተስፋዬ አመልክተዋል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን አርሶ አደሮች የእርሻ መካናይዜሽን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሚንስቴሩ የግብርና መካናይዜሽን ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ሀብቴ ናቸው።

በነዚህም በ2012 ዓ.ም 60 በመቶ የሚሆነው አርሶ አደር በአጨዳ ወቅት የኮምፓይነር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።

የግብርና መካናይዜሽን ልማት ከነበረበት 3 በመቶ ወደ 15 በመቶ ማደጉን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ዘርፉን ለማዘመንና ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሰለጠነውን የሰው ኃይል በማህበር በማደራጀት በስፋት ለማሳተፍ ስትራቴጅ ተነድፎ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

ሀገሪቷ ከደረሰችበት ልማትና ዕድገት አኳያ ከ2 ሺህ 500 በላይ ትራክተሮችና ኮምባይነሮች እንደሚያስፈልጉም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቷ 1 ሺህ 50 ኮምባይነሮችና 750 ትራክተሮች የግብርና መካናይዜሽን አገልግሎት በመስጣት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የአርሲ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መላኩ ታምሩ በበኩላቸው በዘንድሮ ዓመት በዞኑ 56 የእርሻ ትራክተሮች በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች መሰጠቱን ገልጸዋል።

ወጣቶቹ ከዞኑ መስተዳደር የተሰጣቸውን ከ3 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በትራክተር ታግዘው እያለሙ ከመሆን ባለፈ ለአካባቢው አርሶ አደሮች የኪራይ አገልግሎት በመስጠት አማራጭ ገቢ እየፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በማህበር ተደራጅተው በዘርፉ ከተሰማሩት ወጣቶች መካከል ወጣት በፍቀደ ኃይለገብርኤል ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ በእጽዋት ሳይንስ ተመርቆ ከአንድ ዓመት በላይ ሥራ ሲፈልግ እንደነበር አስታውሷል።

መንግስት ባመቻቸው የሥራ ዕድል 11 ሆነው የግብርና መካናይዜሽን መሳሪያ አገልግሎት ለአርሶ አደሩ ለመስጠት መደራጀታቸውን ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚንስቴር አንድ የእርሻ ትራክተር ማግኘታቸውንና በቀጣይ ለአርሶ አደሩ አገልግሎቱን በኪራይ ለመስጠትና ለመለወጥ እንደሚሰሩ አመልክቷል።

የካቲት 20/2010/ኢዜአ/